በጅማ ዩኒቨርሲቲ የብሔራዊ ሰላም በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስልጠና ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባባር 15ኛውን ዙር የብሔራዊ ሰላም በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስልጠና ማስጀመሪያ መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ኤፍሬም ዋቅጅራ (ኢ/ር) በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት÷ ዩኒቨርሲቲው “በማህበረሰቡ ውስጥ ነን” በሚለው መሪ ቃሉ መሰረት ለዘላቂ ሰላም እና አብሮነት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።
የሰላም ሚኒስቴር እስካሁን ካሰለጠናቸው ከ80 ሺህ በላይ ወጣቶች መካከል ጅማ ዩኒቨርሲቲ በ11 ዙር ከ19 ሺህ በላይ ሰልጣኞችን ተቀብሎ አሰልጥኗል ብለዋል።
በዛሬው እለት ደግሞ ከ1 ሺህ በላይ ወጣቶችን ተቀብሎ ማሰልጠን መጀመሩን ጠቁመዋል።
የሰላም ሚኒስቴር ብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ድጋፍና ክትትል ዴስክ ሀላፊ ትዛዙ ደለለኝ በበኩላቸው፤ ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከርና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በስልጠናው ወቅት በዋናነት የአዕምሮ ግንባታና የክህሎት ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ገልፀው፤ ስልጠናው ወጣቶች ራሳቸውንና ሌሎችን የመረዳት፣ አብሮ የመኖርና የበጎ ፈቃድ ባህልን እንዲያሳድጉ ያደረጋል ብለዋል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር በክረምቱ ወቅት በ50 ከተሞች ላይ 6 ሺህ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኞችን በማሰማራት በደም ልገሳ፣ በፅዳት፣ በቤት ማደስ፣ በችግኝ ተከላና በማጠናከሪያ ትምህርት ዘመቻዎች ላይ እያሳተፈ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በሁሴን ከድር