Fana: At a Speed of Life!

ከሀገር በተቃርኖ የቆሙ ሌቦችን መረብ የመበጣጠስ ርምጃ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተለያየ ሁኔታ ሙያዊ ሥነ ምግባር በሌላቸው አንዳንድ አመራሮችና ባለሙያዎች የሚፈጸሙ ብልሹ አሰራሮች የሕዝብ ምሬት ምንጭ ሆነው ቀጥለዋል።

ጥቂቶች የራሳቸውን ሃብት ለማጋበስ የዘረጓቸው የስርቆት መረቦችና አፍራሽ የጥቅም ትስስሮች በሀገር ላይ የሚያደርሱት አደጋ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ለዚህም ነው የመደመር መንግሥት ሙስናን ቀድሞ “የብሔራዊ ደህንነት አደጋ” ብሎ የፈረጀው።

የመደመር መንግሥት ችግሩን ከስሩ ለማድረቅ የተለያዩ ርምጃዎችን ባለፉት ስምንት ዓመታት ወስዷል። በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አድርጎ ከማቅረብ እስከ ሀብትን ማሸሽ የደረሱ ጉዳቶችን የሚከላከሉ ህጎች ወጥተዋል።

ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ በማቋቋም ወንጀለኞች እንዲጠየቁ፣ የሀገርና የሕዝብ ሀብት እንዲመለስ የተሰራው ስራም ውጤት ማስመዝገብ ችሏል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን ጨምሮ ሌሎች የተወሰዱ ሀገራዊ ርምጃዎች ስርዓታዊ ሙሰኝነት እንዳይኖር አድርገዋል።

ሆኖም ይህ ከሀሳብ ዐልቦነት እንዲሁም “ከእኔ ብቻ”ራስ ወዳድነት የሚነሳው የሌብነት አባዜ አሁንም ሙሉ በሙሉ አልታከመም።

ዛሬም ለሕዝብ ምሬት ምክንያት የሆኑ፣ ካለእጅ መንሻ አገልግሎትን የማይሰጡ፣ ስልጣናቸውን ማገልገያ ሳይሆን መገልገያ ያደረጉ አንዳንዶች መኖራቸው በተለያየ መልኩ ሲነሳ ይደመጣል፡፡

እነዚህ ሌቦች የራሳቸውን የዘመድና የጥቅም መረብ በመዘርጋት ሀገር ወደ ብልፅግና የምታደርገው ጉዞ በተገቢው ፍጥነት እንዳይሄድ እነቅፋት የሚሆኑ፣ ሕዝብና መንግሥት ያላቸውን ትምምን የሚያላሉ፣ ከሀገር ብሔራዊ ጥቅም ይልቅ የማይጠረቃ ሆዳቸውን ያስቀደሙ ሆነው ዛሬም በጥፋት ተግባራቸው ላይ ናቸው።

ሙስናና ሌብነት የኢኮኖሚ እድገትን የሚያደናቅፉ፣ ማህበራዊ ፍትህን የሚያጎድሉና የሀገራትን ሉዓላዊነትና ህልውና የሚፈታተኑ ተደራራቢ አደጋዎች ናቸው።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አዳጊ ሀገራት ሲፈፀሙ ደግሞ የብዙ ተማሪና ወጣቶችን ህልም የሚነጥቁ፣ ዘመደኝነትና ጎጠኝነትን የሚያነግሱ፣ ፍትሃዊ የሃብትና የጥቅም ክፍፍልን የሚጎዱ ክፉ ደዌዎች ናቸው።

የዓለም አቀፍ ተቋማት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት÷ የሙስና ጉዳት በጥቂት የገንዘብ ምዝበራዎች የሚወሰን ሳይሆን የመላው ዓለም ኢኮኖሚን የሚጎዳ ነው።

እንደ አለም ባንክ እና የተባበሩት መንግሥታት መረጃዎች፣ በየዓመቱ ከ1 ትሪሊየን ዶላር በላይ ጉቦ የሚከፈል ሲሆን፣ ከ2 ነጥብ 6 ትሪሊየን ዶላር በላይ ደግሞ በሙስና ምክንያት ከየሀገራቱ ኢኮኖሚ ይሰረቃል።

ይህም ከዓለም አቀፍ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት ውስጥ ከ5 በመቶ በላይ ይሸፍናል። በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ግምት በአዳጊ ሀገራት በሙስናና በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ምክንያት የሚባክነው ሀብት በርካታ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በህገ ወጥ የገንዘብ ፍሰትና በንግድ ማጭበርበር ለትምህርት ቤቶች፣ ለሆስፒታሎችና ለስራ እድል ፈጠራ ሊውል የሚችል በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚመዘበር ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

በሀገራችን ለዚህ ውድመት ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎችን በተመለከተ የዓለም ባንክ እና የፌደራል የሥነ-ምግባርና የፀረሙስና ኮሚሽን ያጠናቀሯቸው ስትራቴጂካዊ ጥናቶች ሰፊ ማብራሪያ ይሰጣሉ።

የመሬት አስተዳደርና ልማት ዘርፍ ከመሬት ድልድል፣ ከሊዝ ጨረታና ካርታ ዝግጅት ጋር ተያይዞ ሌቦች ከፍተኛ የእጅ መንሻ የሚጠይቁበት ቀዳሚው ዘርፍ ነው። በተመሳሳይ የመንግሥት ግዥና ኮንስትራክሽን ዘርፍ በትላልቅ መሰረተ ልማቶችና ጨረታዎች ላይ በሚፈጸሙ ማጭበርበሮች የሀገር በጀት ይባክናል።

የታክስና ጉምሩክ አስተዳደር በበኩሉ ታክስ በመሰወር ሀገር ማግኘት የሚገባትን ገቢ የሚያሳጣ ሲሆን፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና የፋይናንስ ተቋማት ደግሞ በብድር አሰጣጥና በውጭ ምንዛሪ ድልድል የሚደረጉ ወገንተኝነቶች የሚስተዋሉባቸው ናቸው።

በኢትዮጵያ ሌብነትና ሙስና ከትናንት እስከ ዛሬ በፈተናነት የቀጠሉ ናቸው። ይህን ፈተና ለማስቀረት የተለያዩ ርምጃዎች ተወስደዋል። በቅርቡም የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም ባሳጡ ፈፃሚዎችና አስፈፃሚዎች ላይ ርምጃ መወሰድ ተጀምሯል።

ነገር ግን ህገ ወጥ አሰራርንና ስር የሰደደ ሌብነትን በአንድ ጀምበር ወይም በወቅታዊ ዘመቻዎች ብቻ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት አይቻልም። ስለሆነም የተጀመረው የህግ የበላይነትን የማስከበርና የሌቦችን መረብ የመበጣጠስ ርምጃ ያለ ምንም ርህራሄ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ግልጽነት ያለው የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት፣ የዲጂታል አሰራሮችን በማስፋፋት የሰዎች ንክኪን መቀነስ፣ የዲጂታል ክፍያዎችን ማጠናከር ችግሩን ከስሩ ማድረቅ ይገባል።

የሙስና ጉዳይ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ግን አይደለም። ህዝቡ ጥቆማና መረጃ በመስጠት የቁጥጥር አካል እንዲሆን በማድረግ የሌቦችን በር ሙሉ በሙሉ መዝጋት የሕልውናችን ጉዳይ ሊሆን ይገባል።

በአፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.