የገጠር ሽግግር ለዘላቂ ልማትና ለሁለንተናዊ ዕድገት
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ የገጠሩ ማህበረሰብ እና የግብርናው ዘርፍ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ።
ይሁን እንጂ የገጠር አካባቢዎች በባህላዊ አኗኗር ዘይቤ እና በደካማ መሠረተ ልማት ውስጥ በመቆየታቸው አጠቃላይ የሀገርን ዕድገት ወደኋላ ሲጎትተው ቆይቷል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ የመደመር መንግሥት የገጠር ሽግግርን እንደ ዋነኛ ስትራቴጂ ይዞ እየሠራበት ነው።
በገጠር ሽግግር ስትራቴጂው የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የገጠር ከተሞችን ለመፍጠር፣ የመሠረተ ልማት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እና ከከተማ ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር እየተሠራ ይገኛል፡፡
በገጠር ሽግግር የግብርናውን ዘርፍ ከባህላዊ አሰራር ወደ ዘመናዊ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ምርታማነት ማሸጋገር እየተቻለ ነው።
ምርታማነት ሲያድግ የአርሶ አደሩና የአርብቶ አደሩ ገቢ ከመጨመሩ ባለፈ ለከተማው ማህበረሰብ አስተማማኝ የምግብ ዋስትና ይረጋገጣል። ከዚህ አንጻር በስንዴ ምርታማነት ላይ እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡
ይህ ሂደት ጠንካራ የገጠር-ከተማ ትስስርን ይፈጥራል። ገጠሩ አካባቢ የግብርና ምርቶችንና ጥሬ ዕቃዎችን ለከተማው ገበያ ሲያቀርብ፣ ከተማው ደግሞ የኢንዱስትሪ ምርቶችን፣ ማዳበሪያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ለገጠሩ ያቀርባል። ይህ የጋራ መደጋገፍ የሀገር ውስጥ ንግድን ያነቃቃል።
በገጠር ሽግግር የግብርና ምርቶችን እሴት የሚጨምሩ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ማዕከላት በገጠር መንደሮች አቅራቢያ እንዲስፋፉ ያደርጋል።
ምርቶችን ሳያቀናብሩ በቀጥታ ወደ ሩቅ ከተሞች ከመውሰድ ይልቅ፣ በአቅራቢያው ማቀነባበር የትራንስፖርት ወጪን ይቀንሳል።
ይህ የኢንዱስትሪዎች መንቀሳቀስ ደግሞ ራሳቸውን የቻሉ አዳዲስ የገጠር ከተሞች እንዲፈጠሩ መሰረት ይጥላል። እነዚህ ታዳጊ ከተሞች የንግድና የኢኮኖሚ ማዕከል በመሆን ማህበረሰቡን ያገለግላሉ።
የገጠር ከተሞች መፈጠር መንግሥትና የግል ባለሀብቶች መሠረተ ልማትን በአግባቡና በውጤታማነት እንዲያዳርሱ በር ይከፍታል።
መንገድ፣ ንጹህ ውሃ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል፣ የቴሌኮም አገልግሎት፣ ትምህርት ቤቶችና ጤና ጣቢያዎች በተበታተነ መልኩ ሳይሆን በእነዚህ ማዕከላት ውስጥ በስፋት ይገነባሉ።
ይህም የህዝቡን የኑሮ ደረጃ ያሻሽላል። ከዚህም በላይ በአግሮ-ኢንዱስትሪውና በመሠረተ ልማት ግንባታው ሳቢያ በርካታ ያልተመረቱ የግብርና ስራዎችና ከግብርና ውጭ የሆኑ የሥራ ዕድሎች በአቅራቢያው ይፈጠራሉ።
የገጠር ሽግግር የስራ ዕድልንና ዘመናዊ አገልግሎቶችን በአቅራቢያ ይፈጥራል፡፡ በዚህም ወጣቶች ቀያቸውን ጥለው የመሰደድ ፍላጎታቸው ይቀንሳል። ፍልሰትን ማስቀረት በመቻሉ በትልልቅ ከተሞች ላይ የሚፈጠረውን የህዝብ ብዛትና የቤት እጥረት ጫናዎችን ይቀንሳል።
በምትኩ፣ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ክፍተት ሳይፈጠር በገጠርና በከተማ መካከል የተመጣጠነ እና ፍትሃዊ እድገት እንዲመዘገብ ያደርጋል።
በአጠቃላይ የገጠር ሽግግር የአንድን ሀገር የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወስን ስትራቴጂካዊ ጉዳይ ነው።
የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ፣ አግሮ-ኢንዱስትሪን በመንደሮች አቅራቢያ በማስፋፋት እና አዳዲስ የገጠር ከተሞችን በመፍጠር ረገድ የሚኖረው ሚና ወደር የለውም።
ይህ ሂደት መሠረተ ልማትን በአግባቡ ለማድረስና የስራ ዕድል በመፍጠር የገጠር-ከተማ ፍልሰትን ለመግታት ፍቱን መድሃኒት ነው።
ሀገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እና በገጠርና በከተማ መካከል የተመጣጠነ እድገት እንዲኖር የመደመር መንግሥት እየተገበረ ያለውን የገጠር ሽግግር ፖሊሲዎችን በቁርጠኝነት መተግበር እና መደገፍ ይገባል።