ሀገራዊ ምክክሩ ለዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት ጉልህ ሚና አለው – የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ የምክክሩ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋት እና ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል አሉ የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች።
ነዋሪዎቹ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ÷ ለዓመታት የቆዩ ጥልቅ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊና ትልቅ ዕድል ይፈጥራል።
የምክክር ሒደቱ ሀገሪቱ ከነበረችበት የኃይልና የጠብ ባሕል ወጥታ በሰለጠነ መንገድ ወደ ውይይት፣ መደማመጥ እና መቻቻል መሸጋገሯን የሚያሳይ መሆኑን አንስተዋል።
ልዩነቶችን ጠረጴዛ ዙሪያ አቅርቦ በሰላማዊ መንገድ መነጋገር መጀመሩ ለሀገር ዘላቂ ሰላም፣ ለሕዝቦች አንድነትና ለሁሉን አቀፍ ብልጽግና መሠረት የሚጥል አዎንታዊ ርምጃ ነው ብለዋል።
በሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ሒደት ላይ የሚነሱ ሃሳቦች ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡
በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ ምክክር የተሟላ ፍሬ የሚያፈራው ሁሉም የበኩሉን ሚና ሲወጣ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
በኦሊያድ በዳኔ