አብሮነትና መተሳሰብን የሚያጠናክረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በኦሮሚያ ክልል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዘርፎች የሚሰጠው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በዛሬው ዕለት በጅማ ዞን ማና እና ጎማ ወረዳ ከ5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የተለያየ ዓይነት ድጋፍ ተደርጓል፡፡
ድጋፉ ከተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ አንስቶ ሴቶች በቡድንና በተናጠል ሠርተው ሕይወታቸውን በዘላቂነት የሚደጉሙበት መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የጅማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ትጃኒ ናስር በዚህ ወቅት ÷ የዞኑ ነዋሪዎች እና ባለሃብቶች ሃብት በማሰባሰብ አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በዞኑ 21 ወረዳዎች ውስጥ ከ3 ሺህ በላይ ቤቶች ለአቅመ ደካሞች መገንባታቸውን ጠቅሰው ÷ አብሮነትን የሚያጠናክሩ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በገንዘብ የማይተመን ሰብዓዊ ተግባር ነው ያሉት አስተዳዳሪው ÷ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የወጣቶች ክንፍ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ረሂማ ዩሱፍ በበኩላቸው ÷ በክልሉ በርካቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን አመልክተዋል፡፡
በበጎ ፈቃድ ሥራው የወጣቶች ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ÷ ሁሉም ዜጋ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚያደርገውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡
በወርቃፈራሁ ያለው