የአፍሪካ ከተሞች የከንቲባነት አመራር መርሐ ግብር በኢትዮጵያ ከተሞች ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ጀምሯል – ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ከተሞች የከንቲባነት አመራር መርሐ ግብር በኢትዮጵያ ከተሞች ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ጀምሯል አሉ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፡፡
ሚኒስትሯ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ከአፍሪካ ከተሞች የከንቲባነት አመራር መርሐ ግብር ዋና ዳይሬክተር ጃኒ ካማሊ ጋር በፕሮግራሙ ጠቀሜታ፣ በጎ ተጽዕኖና ቀጣይነት ዙሪያ መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ከተሞች ከንቲቦች ፎረምን እንድታስተናግድ መመረጧን ገልጸው፥ ፕሮግራሙ በሀገራችን ከተሞች የአመራር አቅም ግንባታና ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ከጀመረ 4 ዓመታትን አስቆጥሯል ብለዋል፡፡
በዋናነት ዘላቂ አሻራ ያለው የከንቲባነት አመራር በመፍጠር፣ የከተሞችን ዲጂታላይዜሽን እና የዳታ አስተዳደር በማዘመን፣ ከተሞች የውስጥ ገቢያቸውን አጎልብተው በራስ አቅም እንዲለሙ በማስቻል ረገድ ትልቅ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
በመጪው ጥቅምት ወር በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ ከተሞች የሚካሄደውን ይህን ታላቅ የአፍሪካ ከንቲቦች ዳግም ፎረም ስኬታማ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡