የኢትዮጵያ እና ኬንያን ወታደራዊ ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ረጅም ዓመታት ያስቆጠረውን ኢትዮጵያ እና ኬንያ ወታደራዊ ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ጄነራል ባጫ ደበሌ ከሀገሪቱ ጦር ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ቻርሊስ ካሃሪሪ ጋር በሀገራቱ የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል፡፡
የሁለቱ ወገኖች ውይይት በዋናነት የሀገራቱን ወታደራዊ ግንኙነትና ሁለንተናዊ ወዳጅነት አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ እና ኬንያ ወታደራዊ ትብብር መጠናከር ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ ሀገራቱ በሚጋሯቸው የድንበር አካባቢዎች የጸጥታና ደህንነት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በሀገራቱ ወታደራዊ ተቋማት መካከል በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ የሚደረጉ ውይይቶች በመደበኛነት ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ እና ኬንያ መካከል ያለው አጋርነት መጠናከር የአፍሪካ ቀንድን ደህንነት፣ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተገልጿል።