ኢትዮጵያ ስብራቶቿን በምክክሩ አክማ ለማዳን ዝግጅቷን እየጨረሰች ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና መዋቅራዊ ስብራቶችን አሳልፋለች።
እነዚህን የረጅም ዘመናት ውስብስብ ችግሮች በዘላቂነት ለማከም እና የጋራ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እየተካሄደ ያለው ሁሉን አካታች ሀገራዊ ምክክር ዋነኛ መፍትሄ ነው፡፡
በዚሁ መሠረት በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስተባባሪነት በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈው ሀገራዊ ምክክር ፍሬ እያፈራ ነው፡፡
ይህ ታሪካዊ መድረክ በሀገሪቱ ውስጥ ለዘመናት አወዛጋቢ በነበሩ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ በነጻነት በመወያየት አዲስ የሰላምና የአንድነት ምዕራፍ ለመክፈት እያገዘ ይገኛል፡፡
ኮሚሽኑ ባለፉት አራት ዓመታት ከመላው ሀገሪቱና ከሀገር ውጭ ከሚገኙ ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች ያሰባሰባቸውን ግብዓቶች መሠረት በማድረግ ስምንት ዋና ዋና አጀንዳዎችን ለይቶ ይፋ በማድረግ ተመካካሪዎች ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ እየመከሩባቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ዛሬ የምክክር ኮሚሽኑ በስምንት የአጀንዳ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሲመካከሩ የቆዩት የአጀንዳ ቡድኖች መግባባት ላይ መድረሳቸውን አሳውቋል፡፡
ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ በሰላም ግንባታ፣ በሃይማኖት ጉዳዮች፣ በሙስና እና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በመንግሥት አደረጃጀት እና የፖለቲካ ስርዓት ላይ ሲመካከሩ የነበሩ ቡድኖች መግባባት ላይ እንደደረሱ መግለፁ የሚታወስ ነው፡፡
በዛሬው ዕለት ደግሞ በሀገር ግንባታ፣ በፌዴራል ከተሞች ጉዳይ፣ በተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት እና ሰብዓዊ መብት እንዲሁም በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ተመካካሪዎች ከስምምነት መድረሳቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሳውቋል፡፡
መግባባት ላይ የተደረሰባቸው ስምንቱ አጀንዳዎች ወደፊት በተግባራዊ የህግ፣ የመዋቅር እና የፖለቲካ ማሻሻያዎች ታግዘው ወደ ተግባር ሲቀየሩ የኢትዮጵያን የረጅም ዘመናት ስብራቶች ለማከም እውነተኛና ዘላቂ መፍትሄዎች ይሆናሉ፡፡
በአጠቃላይ ምክክሩ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት የመፍታት አዲስ ባህልን እያስተማረ ይገኛል።