Fana: At a Speed of Life!

የካይሮ የጥፋት ተልዕኮ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሌሎች ሀገራት ጥፋት ላይ ጥቅምን ለማስከበር የሚታትረው የካይሮ የጥፋት ተልዕኮ ከአፍሪካ ቀንድ ትርምስ ጀርባ የሴራ መረቡን ዘርግቶ ደም ማቃባት ከጀመረ ዓመታትን ቆጥሯል።

የካይሮ የጥፋት ተልዕኮ መነሻው ምክንያታዊ ያልሆነ ግትርነት መዳረሻው ደግሞ ጥፋት እና የሀገራትን የብልፅግና ጉዞ ማጨናገፍ ነው።

የዚህ ሴራ ገፈት ቀማሽ የሆነችው ሱዳን በካይሮ የጥፋት በትር ዋጋ ከሚከፍሉት ሀገራት መካከል አንዷ እና የቀጣናው ማሳያ ተደርጋ የምትወሰድ ናት።

ለቀውሱ ጭድ እና ክብሪት አቃብላ ከዳር የምትሞቀው ግብፅ በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ላይ ያላት አግድም ዕይታ የቀጣናው ቀውስ ምክንያት እንድትሆን አድርጓታል።

ከተፈጥሮም ሆነ ከዓለም አቀፍ ሕግም በተቃርኖ የምትቆመው ግብፅ በዓባይ ወንዝ ጉዳይ የቅኝ ግዛት ዘመን ሰምምነቶችን በመጥቀስ ታሪካዊ ባለርስት ነኝ ባይ ናት።

ይህ አይደለም በዚህ ዘመን ያኔ እንኳ በቀኝ ገዢዎቻቸው ዕሳቤም ፍትሐዊ እንዳልሆነ በውል የሚረዱት ዕውነት ሆኖ ሳለ “አይናችሁን ይዤ ላሞኛችሁ” ዓይነት የካይሮ ጨዋታ ግን አሁንም አቋሙን አልቀየረም፡፡

ለዚህም ነው በቀንዱ ስውር ደባ ደም የማቃባት ግብሯን በቅጥረኞቿ እና ክብራቸውን በካይሮ ችሮታ በለወጡ ባንዳዎች ተልዕኮዋን የምትፈፅመው።

ለሱዳን ከእኔ በላይ ላሳር ባይ፣አዛኝ ቅቤ አንጓችም ሆና በመንታ መልክ ከካርቱም ውድቀት ጀርባ ያደባችው ግብፅ ከሰሞኑ የፈፀመችው ጥቃት የዕብለቷ ማሳያ ሆኖ ሊጠቀስ የሚችል ነው።

በወርቅ ምርት ከአፍሪካ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የምትሰለፈው ካርቱም ትልቁን ገቢ የምታገኝበትን ዋነኛውን የወርቅ ማምረቻ አለሁልሽ ባለቻት የቅርብ ወዳጅ ሆና በቀረበቻት ግብፅ ዶግ አመድ ሆኖባታል።

ይህን ክስተት ሬውተርስና ዊዎን የዜና ምንጭ በሳተላይት ምስል በመታገዝ የዘገቡት ሲሆን÷ ግብፅ ከክስተቱ ጀርባ መኖሯን እንዲሁም የካርቱም ቀውስ እና የቀጣናው አለመረጋጋት የካይሮ ጣልቃገብነት እንዳለበት አረጋግጧል፡፡

በተመሳሳይም የካርቱሙ የካይሮ የጥፋት ተልዕኮ አንድ እግሩን አስመራ አድርጎ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ለመቆም እየተውተረተረ ይገኛል፡፡

ይህ ኢትዮጵያን እንደ ሱዳን አዲስ አበባን እንደካርቱም የማድረግ ጉዙ “ፅምዶ” በሚል ያልተቀደሰ ጋብቻ የተሳሰረ ነው፡፡

ሆኖም ግን ደመና ትልሙን፣ጉም ሀሳቡን ገቢራዊ ያደርግ ዘንድ አቅም የለውም ፤ ኢትዮጵያ ሱዳን አይደለችም፤ አዲስ አበባም ካርቱም አትሆንም፡፡

በወንድሙ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.