የባሕር በር ተጠቃሚነት ለቀጣናዊ ኢኮኖሚ እድገት
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕር በር ተጠቃሚ መሆን ከኢኮኖሚ፣ ከንግድ፣ ከደህንነት እና ከዓለም አቀፍ ግንኙነት አንፃር እጅግ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡
የባሕር በር ባለቤትነትን ማረጋገጥ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ እና ጂኦፖለቲካዊ ግንኙነት ውስጥ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ አይደለም።
በታሪክ አጋጣሚዎች እንደተስተዋለው የባሕር በር ባለቤት የሆኑ ሀገራት ከኢኮኖሚ እድገታቸው ባለፈ በአካባቢያቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ፣ የደህንነት እና የዲፕሎማሲያዊ ተጽእኖ የመፍጠር አቅም ይኖራቸዋል፡፡
የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ለመድረስ በባሕር ባለቤት ሀገራት ላይ ጥገኛ ይሆናሉ።
ይህ ጥገኝነት የባሕር በር ባለቤት የሆኑ ሀገራት በታሪፍ፣ በወደብ አገልግሎት ክፍያ እና በትራንዚት ህጎች በኩል በጎረቤቶቻቸው ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ተጽእኖ እንዲኖራቸው ያደርጋል።
የባሕር መውጫ በር ያላቸው ሀገራት በችግር ጊዜ የውጭ ንግዳቸውን እና የነዳጅ አቅርቦታቸውን ያለ ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ማስቀጠል ይችላሉ፤ ይህም የፖለቲካ ነጻነታቸውን ያጠናክራል።
የባሕር በር ባለቤትነት ጠንካራ የባሕር ኃይል ለመገንባት እና በአካባቢው የሚገኙ የባህር አካላትን ለመጠበቅ ያስችላል። ይህ አቅም ስጋቶችን ከሩቅ ለመግታት እና በክልላዊ የደህንነት ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ተሳታፊ ለመሆን ይረዳል።
እንደ ባብ ኤል-መንደብ፣ የሱዊዝ ካናል ወይም የሆርሙዝ ሰርጥ ባሉ ወሳኝ የባሕር መስመሮች አቅራቢያ የሚገኙ ሀገራት ዓለም አቀፉን የንግድ እንቅስቃሴ በንቃት የመከታተልና የመቆጣጠር አቅም ስለሚያገኙ ከሌሎች የዓለም ሀገራት ጋር ያላቸውን የመደራደር አቅም ከፍ ያደርጋል።
የባሕር በር የሌላቸውን ሀገራት የንግድ መስመር በመፍቀድ ወይም በመከልከል ረገድ የሚደረጉ ስምምነቶች ብዙውን ጊዜ ከፖለቲካዊ እና ከደህንነት ትብብር ቅድመ-ሁኔታዎች ጋር ይያያዛሉ።
በቀጣናዊ የትብብር ማዕቀፎች ውስጥ የባሕር በር ያላቸው ሀገራት የኢኮኖሚ እና የትራንስፖርት ትስስር ማዕከል በመሆናቸው የፖለቲካ ውሳኔዎችን ከራሳቸው ጥቅም ጋር ለመዋጀት አመቺ ይሆንላቸዋል።
የባሕር በር ያላቸው ሀገራት በንግድ፣ በደህንነት እና በዲፕሎማሲ መስክ ያሏቸው እድሎች በጎረቤቶቻቸው እና በዓለም አቀፍ አካላት ዘንድ ያላቸውን ፖለቲካዊ የመደራደር አቅም በከፍተኛ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል።
የባሕር በር ለሀገራት የኢኮኖሚ እድገት፣ የንግድ መስፋፋት፣ የኢንዱስትሪ ልማት፣ የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብ እና የክልላዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ አለው።
ኢትዮጵያ የባሕር በር በማጣቷ ከፍተኛ የማጓጓዣ ወጪ፣ የውጭ ጥገኝነት፣ የምርት ዋጋ መጨመር፣ የብሔራዊ ደህንነት እና የኢንቨስትመንት ተግዳሮቶችን ተጋፍጣለች።
ኢትዮጵያ የምታነሳው ሕጋዊና ፍትሃዊ የባሕር በር ባለቤትነት መብት ጥያቄም የድንበር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የብሄራዊ ጥቅም፣ የሀገር ሉዓላዊነት እና ሕልውናን የማስከበር ጉዳይ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በዘላቂነት የባሕር በር ተዘግቶባት መቀጠል እንደማትችል በመገንዘብ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ የሀገሪቱን ፍትሃዊ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መስራት የሚጠበቅበት ሲሆን÷ መላው ኢትዮጵያውያንም ይህ ቁልፍ ብሔራዊ ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ በአንድነት መቆም አለባቸው፡፡