Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ቱሪዝም ስትራቴጂክ የብሪክስ ትብብር መስክ እንዲሆን ጥሪ አቀረበች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ያሏትን የቱሪዝም እና የስፖርት ፀጋዎች ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ስትራቴጂካዊ ጥሪ በብሪክስ መድረክ ላይ አቅርባለች፡፡
ኢትዮጵያ በህንድ ጃይፑር በተካሄደው የቱሪዝም ሚኒስትሮች ስብሰባ እና በስፖርት ሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ በመገኘት፣ አባል ሀገራቱ በተጨባጭ ተግባራት ላይ ያተኮረ ትብብር እንዲያደርጉ ሐሳብ አቅርባለች።
በመድረኩ ላይ የተገኘው የኢትዮጵያ ልዑክ፣ ሀገራችን “የሰው ዘር መገኛ” እንደመሆኗ ያሏትን ድንቅ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶች በማስተዋወቅ በዘርፉ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በቱሪዝም ዘርፍ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ፣ የዲጂታል ፈጠራ እና የክህሎት ማሳደግ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኗን አብራርቷል፡፡
በመድረኩ ኢትዮጵያ የብሪክስ የጉዞ ማዕከል እና የቱሪዝም የልህቀት ማዕከል እንዲቋቋሙ የቀረቡት ሐሳቦች የኢትዮጵያን መሪነት አሳይተዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከብሪክስ ሀገራት ጋር በማገናኘት ረገድ ያለውን ሚና እና አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ማዕከል የመሆን አቅሟ ለተሳታፊዎች ቀርቧል።
ኢትዮጵያ በረጅም ርቀት ሩጫ ያላትን ዝና ወደ ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ትብብር ለመቀየር የስፖርት ሳይንስና ልማት ዘርፍ በአትሌቶች ልማት እና በስፖርት ሳይንስ ዙሪያ የላቀ የጋራ ሥራ እንዲኖር ጠይቃለች።
የሴቶች፣ የወጣቶች እና የአካል ጉዳተኞች በስፖርት ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ እንዲሁም ባህላዊ ስፖርቶች እንዲስፋፉ ጥሪ በማቅረብም ስፖርት ለኢኮኖሚ እድገትና ለኢንቨስትመንት ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ፣ ተግባራዊ የሆነ “የብሪክስ ስፖርት ትብብር ማዕቀፍ” እንዲኖር ሐሳብ አቅርባለች።
ኢትዮጵያ እነዚህን የትብብር ሐሳቦች ወደ ተጨባጭ ተግባር በመለወጥ፣ ለዜጎቿ አዲስ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር ሙሉ ዝግጁነቷን አረጋግጣለች።
በህንድ የኢትዮጵያ ኢምባሲ መረጃ እንዳመላከተው÷ኢትዮጵያ በብሪክስ አባልነቷ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ አድማሷን ለማስፋት በቁርጠኝነት እየሠራች ትገኛለች፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.