የመውሊድ በዓል በታላቁ አንዋር መስጂድ በድምቀት እየተከበረ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 1ሺህ 501ኛው የነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት በዓል (መውሊድ) በታላቁ አንዋር መስጂድ “የፍትሁ ነቢይ” በሚል መሪ ቃል በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዚዳንት ሼህ አብዱልከሪም በድረዲን ባስተላለፉት መልዕክት፥ በዓሉ በርካታ ሂደቶችን አልፎ የጋራ ምክረ ሀሳብ በማቅረብ በተጠናቀቀው ሀገራዊ ምክክር ማግስት የሚከበር መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ነብዩ መሐመድ የሐበሻን ታላቅነት መመስከራቸውን በማውሳት፤ ሕዝበ ሙስሊሙ ለሀገራችን ሰላምና አንድነት ሊተጋ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የነቢዩ መሀመድን (ሰ.ዐ.ወ) የልደት በዓል ስናከበር ዓመቱን ሙሉ የእርሳቸውን ሱና እንዲሁም አስተምህሯቸውን በመተግበር፣ ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በማሰብና በማገዝ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
በታላቁ አንዋር መስኪድ ወጣት ጀመአ አስተባባሪነት በተለያዩ ቦታዎች ከ6 ሺህ በላይ ድጋፍ የሚሹ ወገኖች የምገባ መርሐ ግብር መዘጋጀቱ ተመላክቷል።
በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት እንዲሁም የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ኃላፊዎች፣ የታላቁ አንዋር መስጂድ ዋና ኢማም ሼህ ጠሀ መሐመድን ጨምሮ ዲፕሎማቶችና በርካታ የእምነቱ ተከታዮች ተገኝተዋል።
በሔኖክ ለሜ