በኦሮሚያ ክልል ከመኸር ሰብል ከ380 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ከመኸር ሰብል ከ380 ሚሊየን 6መቶ ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው አሉ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ።
ኃላፊው እንዳሉት፥ በክልሉ ከመኸር አዝመራ የተሻለ ምርት በመሰብሰብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።
ለምርት ዘመኑ የእርሻ መሬትን በአግባቡ አዘጋጅቶና ግብአቶችን ተጠቅሞ በዘር ከመሸፈን በመቀጠል ሰብሉን ከአረም፣ ከነፍሳትና ከተለያዩ በሽታዎች መከላከል ወሳኝ መሆኑን በማንሳት አርሶ አደሩን ዘመናዊና ባህላዊ የሰብል ጥበቃ ዘዴዎችን አቀናጅቶ እንዲጠቀም ባለሙያዎችን መድቦ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም በክልሉ በምርት ዘመኑ ከ11 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬትን በማልማት ከ380 ሚሊየን 6 መቶ ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥም እስካሁን 9 ሚሊዮን 627 ሺህ 749 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈኑን አመልክተዋል።
በተጨማሪም ምርታማነትን ለመጨመር የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ ከ5 ሚሊየን በላይ ሄክታር መሬት በትራክተር መታረሱን አስረድተዋል።
ከግብዓት አቅርቦት አንጻርም ከቀረበው ከ10 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን ከ7 ሚሊየን 677 ሺህ ኩንታል በላይ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን እና የአረም እና ተባይ ማጥፊያ ኬሚካሎችም ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጩ መደረጉን ጠቁመዋል።
በዚህም በተቀናጀና በተናበበ አሰራር በተከናወኑ ስራዎች በአሁኑ ወቅት የሰብሉ ቁመና በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡