Fana: At a Speed of Life!

በበጀት አመቱ ከ2 ቢሊየን 823 ሚሊየን በላይ ኪሎ ዋት ስዓት የኢነርጂ ሃይል ብክነትን በመቀነስ 1 ቢሊየን ብር ማዳን ተቻለ

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 27 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበጀት አመቱ ከ2 ቢሊየን 823 ሚሊየን በላይ ኪሎ ዋት ስዓት የኢነርጂ ሃይል ብክነት መቀነስ መቻሉ አስታወቀ።

የኤሌክትሪክ ኃይል በዋነኛነት ቴክኒካል እና ቴክኒካል ባልሆነ በሁለት አይነት መንገዶች ብክነት ሊከሰት እንደሚችል ተገልጿል።

በዚህም የቴክኒካል የሃይል ብክነት ከኤሌክትሪክ ማሰራጫና ማከፋፈያ መስመር እርጅና፣ ከኔትወርክ አቅም ውስንነት፣ ከመሰረተ-ልማት ጥራት ችግር፣ ከዲዛይን እና ከኢንጂነሪንግ የአሰራር ክፍተት የሚፈጠር ነው።

ከዚያም ባለፈ ወቅታዊና ትክክለኛ የቆጣሪን ንባብ ካለመውሰድ፣ ከቢሊን ስርዓቱ አለመዘመን፣ ወቅታዊና ትክክለኛ ንባብ ወደ ሲስተም ካለማስገባት፣ ክፍያ ሳይፈፅሙ በሚጠቀሙ ደንበኞች፣ የማይቆጥሩ ወይም የተበላሹ ቆጣሪዎች መኖር፣ ከኢነርጂ ስርቆት እና ከአሠራር ክትትል ክፍተት የሚፈጠር ብክነት ደግሞ ቴክኒካል ያልሆነ ወይም ኮሜርሻል የሃይል ብክነት ይባላልም ነው ያለው ተቋሙ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም በ2012 በጀት አመት በሁለቱ መንገድ ሊከሰት የሚችለውን የሃይል ብክነትን ለመከላከል ባደረገው የክትትልና ቁጥጥር ስራ 2 ቢሊየን 823 ሚሊየን 055 ሺህ 758 ኪሎ ዋት ስዓት የኢነርጂ ሃይል ብክነት በመቀነስ 1 ቢሊየን 113 ሚሊየን 863 ሺህ 407 ብር ከብክነት ማዳን መቻሉን ገልጿል።

ተቋሙ የሃይል ብክነቱን መቀነስ የቻለው÷ የኤሌክትሪክ ስርቆትን በመከላከል፣ በትክክል የማይሰሩ፣ የተቃጠሉ፤ የቆሙ ቆጣሪዎች በወቅቱ እንዲቀየሩ በማድረግ፣ የታሪፍ ለውጥ የሚያስፈልጋቸውን ደንበኞች የታሪፍ ለውጥ በማድረግ፣ ቢል የማይወጣላቸው ደንበኞችን ወደ ሲስተም እንደገቡ በማድረግ፣ ያልተፈቀደ የኃይል ጭነት በመቆጣጠር እና በመሳሰሉት መሆኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ተቋሙ ቴክኒካል የሃይል ብክነትን ለመቀነስም የተለያዩ ስራዎች ሲያከናውን መቆየቱን በመግለፅ ፤ በ2013 በጀት አመትም ሊከሰቱ የሚችሉ ቴክኒካልና ቴክኒካል ያልሆኑ የሃይል ብክነቶችን ለመቀነስ ሰፊ እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.