በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ 290 ትምህርት ቤቶች ተገንብተዋል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ 4 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ 290 ትምህርት ቤቶች መገንባት ተችሏል አለ የክልሉ ትምህርት ቢሮ፡፡
3ኛው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የትምህርት ጉባኤ ዘላቂ የትምህርት ጥራት ለላቀ የመማር ውጤትና ብልጽግና በሚል መሪ ሀሳብ በሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ የትምህርት ቤቶች ግንባታ ስራዎች ማህበረሰቡ ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል፡፡
በክልሉ የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ባለፉት ሦስት አመታት 4 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የሚገመት ሀብት ማሰባሰብ መቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህም 290 አዳዲስ ትምርህት ቤቶችና 2ሺህ 792 አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች መገንባታቸውን አመልከተዋል፡፡
10 ሺህ 92 የመማሪያ ክፍሎች ጥገና መደረጉንና 72 ሺህ 863 የተማሪዎች መቀመጫ ወንበሮች ተገዝተው ለትምህርት ቤቶች መቅረባቸውንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የትምህርት ተደራሽነትን እውን ለማድረግ ከማህበረሰቡ ጋር በተሰራው ስራ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በ2016 ከነበረበት 1ሺህ 775 በዘንድሮ ዓመት ወደ 2ሺህ 219 ማሳደግ መቻሉን አንስተዋል፡፡
በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በክልሉ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች መካከል 61 ነጥብ 4 በመቶ ያህሉ በበይነ መረብ መፈተናቸውን አስታውሰው፤ በ2019 የትምህርት ዘመን ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ ለመስጠት መታቀዱን አመልክተዋል፡፡
ከመድረኩ ጎን ለጎን ባለፉት ሦስት አመታት በትምህርት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራትን የሚያሳይ የፎቶ አውደ ርዕይና የተማሪዎችና መምህራን የፈጠራ ስራዎች ጉብኝት ተደርጓል።
በመድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰውን (ዶ/ር) ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
በጥላሁን ይልማ