Fana: At a Speed of Life!

ለኢኮኖሚ እድገት አዲስ ተስፋ የፈነጠቀው የማዕድን ዘርፍ ማንሠራራት

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እጅግ በርካታ የማዕድን ሃብት ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም ቀደም ባሉት ጊዜያት ይህንን እምቅ ሃብት በአግባቡ አልምቶ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት እንዲያበረክት የማድረግ አቅሟ አመርቂ አልነበረም።
ባለፉት አምስት ዓመታት ግን የመደመር መንግሥት ለዘርፉ ባከናወናቸው ተግባራት ነገሮች ተቀይረዋል፡፡
የመደመር መንግሥት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳው ውስጥ ማዕድንን አንዱ መሠረታዊ የኢኮኖሚ ልማት ምሰሶ ማድረጉ፣ ለዘርፉ ፈጣን ዕድገትና ለባለሃብቶች ምቹ ምሕዳርን ፈጥሯል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተጨባጭ ከተመዘገቡ አስደናቂ ስኬቶች መካከል አንዱ የሆነው የወርቅ ምርት በ2018 በጀት ዓመት 5 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ገቢ በማስገኘት ትልቅ ታሪካዊ እመርታ አሳይቷል።
በዚህም በአንድ ዓመት የተገኘው የወርቅ ገቢ ከለውጡ በፊት በነበሩ 27 ዓመታት ከተሰበሰበው አጠቃላይ ሃብት በላይ ሆኗል፡፡
ይህ ስኬት የመጣው በሕገ ወጥ መንገድ የሀገር ሀብት ወደ ግል ኪስ እንዳይገባ በመደረጉ እና የወርቅ ሃብትን በአግባቡ መጠቀም በመቻሉ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የወርቅ ጉዞ በጥሬው ማዕድን በመሸጥ ብቻ የሚቆም አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ታሪኳን በመቀየር የመጀመሪያውን ግዙፍ የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካ በመገንባት ላይ ትገኛለች።
ቀደም ሲል ማዕድናት በጥሬው ወደ ውጭ ይላኩ ከነበረበት አሠራር በመውጣት፣ አሁን ላይ እንደ ወርቅ፣ ድንጋይ ከሰል፣ ኦፓልና ሌሎች ጌጣጌጦች ላይ እሴት ተጨምሮባቸው ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡበት ስኬታማ አሠራር ተዘርግቷል።
የሲሚንቶ ምርትም እንዲሁ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ6 ነጥብ 2 ሚሊየን ቶን ወደ 10 ነጥብ 4 ሚሊየን ቶን አድጓል።
በጥራት ደረጃ እሴት የተጨመረበት የድንጋይ ከሰል ምርትም ለሀገር ውስጥ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚያስፈልገውን ግብዓት እስከ 75 በመቶ መሸፈን የሚያስችል ትልቅ አቅም ፈጥሯል።
በአብዛኛው ከውጭ ይገባ የነበረውን የሴራሚክ ምርት በሀገር ውስጥ የማምረት አቅም በማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን መሸፈንና ለግዢ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ተችሏል።
ይህ ሁሉ ስኬት የተገኘው የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪው ውስጥ በስፋት እንዲሰማሩ የሚያግዙ ምቹ ፖሊሲዎችና የአሰራር ሥርዓቶች በመሻሻላቸው ነው።
የማዕድን ዘርፍ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለተኪ ምርት ዕድገት እና የውጭ ምንዛሪን ለማዳን እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነው።
እስካሁን በታዩ አመርቂ ውጤቶች መነሻነት የማዕድን ዘርፉ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ማንሠራራት የሚጫወተው ሚና ይበልጥ እያደገ እንደሚሄድ ይጠበቃል፡፡
በምሕረት ደምሴ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.