ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት የተጀመረው ጉዞ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከዘመን መለወጫ በዓል ደስታና መታደስ ቀጥሎ በሚመጡት የስራ ቀናት በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙ ተማሪዎች ለ2019 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ወደ ትምህርት ገበታቸው ይመለሳሉ፡፡
የ2019 የትምህርት ዘመን በይፋ ተጀምሯል። የትምህርት ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ባለፉት ዓመታት የመደመር መንግሥት በትምህርት ዘርፍ ዘላቂና መዋቅራዊ ለውጦችን ለማምጣት ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
ትምህርትን የትውልድ መገንቢያና የሀገር እድገት መሠረት በማድረግ በተሰሩት ሥራዎች በየዘርፉ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
ባለፉት ዓመታት በትምህርት ዘርፉ የተከናወኑት ሀገራዊ የሪፎርም ስራዎች ተማሪን ወደ ትምህርት ቤት ከመላክ ባሻገር፤ ዘመኑን የሚመጥን ዓለም አቀፋዊ ብቃት እና ክህሎት ያለውን ባለርዕይ ትውልድ ለማፍራት ያለሙ ናቸው።
በየደረጃው የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች የትምህርት እድል እንዲያገኙ ለማስቻል ሰፊ የትምህርት መሠረተ ልማት ዝርጋታ ተካሂዷል፡፡
በሁሉም ክልሎች የላቀ ብቃት ያላቸውን ተማሪዎች ለማፍራት የሚያስችሉ አዳሪና የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤቶች ተገንብተው ሥራ ጀምረዋል።
የትምህርት ቤቶችን የቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ የኮምፒውተር ላቦራቶሪዎች፣ የኢንተርኔት ዝርጋታ እና የዲጂታል መማሪያ መጻሕፍት ስርጭት በሰፊው ተከናውኗል፡፡
የቅድመ መደበኛና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻልና ትምህርት ቤቶችን ለህብረተሰቡ ቅርብ በሆነ ቦታ የመገንባት ሥራ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መስራት ተችሏል።
የመምህራንን ሙያዊ ብቃት ለማሳደግ የማዕቀፍ ስልጠናዎች፣ የሙያ ፈቃድ ምዘናዎችና የከፍተኛ ትምህርት እድሎች በማመቻቸት ረገድ ዘረትፈ ብዙ ሰራዎች ተሰርተዋል፡፡
በመደመር መንግሥት ቅድሚያ ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነው የትምህርት ዘርፍ፤ በመዋቅራዊ ለውጦች የመማር ማስተማር ደረጃው በላቀ ደረጃ ተሻሽሏል፡፡
በዚህም በተደረገው የካሪኩለም ማሻሻያ ዲጂታል የእውቀት ሽግግርን የሚያስቀድም ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓት ተተግብሯል።
የዩኒቨርሲቲ መውጫ እና መግቢያ ፈተናዎች ተተግብረው ጥረት እና ብቃት ዋጋ የሚያገኙበት ሥርዓት ተዘርግቷል።
ሀገር በቀል እውቀትን፣ ተግባር ተኮር ትምህርትንና የቴክኖሎጂ ክህሎትን ያካተተው አዲሱ ካሪኩለም ተወዳዳሪና እውቀት መር ትውልድ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መሰረት ጥሏል፡፡
የትምህርት ጥራት ማረጋገጫ ከሆኑት ዋና ዋና ማዕቀፎች አንዱ የምዘና ስርዓት ማሻሻል እንደመሆኑ ፈተናን በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መስጠት መጀመሩና የዲጂታል (ኦንላይን) ፈተና ስርዓት መተግበሩ የፈተና ስርቆትን እና ኩረጃን ማስቀረት አስችሏል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች የሙያ ብቃታቸው ተረጋግጦ እንዲወጡ የተደረገው አሰራር የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን ወደ አዲስ ደረጃ አሸጋግሮታል፡፡
ትምህርት የጋራ ኃላፊነት እንደመሆኑ ወላጆች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች እና መላው ማህበረሰብ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የሚጠበቅበትን ድርሻ መወጣት ይጠበቅበታል፡፡
በምሕረት ደምሴ