Fana: At a Speed of Life!

ብቃት ያለው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመቅረጽ የተጀመሩ የትምህርት ዘርፍ የለውጥ ርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ብቃት ያለው ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመቅረጽ የተጀመሩ የለውጥ ርምጃዎች ተጨባጭ ውጤት እያስገኙ ነው አለ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)።

ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ የትምህርት መሰረተ ልማትን ለማሻሻል በተጀመረው ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ እና የትምህርት ሥርዓት ሪፎርሞች አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።

የለውጡ ዋና ዓላማ ከቅድመ-መደበኛ፣ ከ1ኛ ደረጃ እና ከ2ኛ ደረጃ ጀምሮ በራስ መተማመን ያለው አዲስ ትውልድ መገንባት መሆኑንም አብራርተዋል።

የሪፎርሙ ውጤት በሂደት እየታየ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት የትምህርት ጥራት እየተሻሻለ መምጣቱንና ትክክለኛ አቅም ያላቸው ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ እየገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በሀገር አቀፍ የ12ኛ ክፍል ፈተና ላይ የተደረገው የትምህርት ዘርፍ ሪፎርም የተማሪዎችን ውጤትና አጠቃላይ የትምህርት ጥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለው መጥቷል ነው ያሉት፡፡

በቀጣይም ተማሪዎች ከዚሁ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን የቴክኒክና ሙያ ትምህርቶችንም ጭምር እንዲያስተምሩ የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል።

ይህ የተቀናጀ የትምህርት ሥርዓት ተጠናክሮ ሲቀጥል፤ በጽኑ መሰረት ላይ የቆመና የነገዋን ሀገር በብቃት መሸከም የሚችል አዲስ ትውልድ ማፍራት እንደሚያስችል ታምኖበታል ብለዋል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በተከናወነው የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ አማካኝነት በገንዘብና በአይነት በርካታ ሀብት ከህብረተሰቡና ከባለድርሻ አካላት ተሰብስቧል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ይህ ንቅናቄ የትምህርት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የመንግሥት ጥረት ብቻ ሳይሆን፤ የህብረተሰቡና የወላጆች ንቁ ተሳትፎ የታየበት ትልቅ ርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ወደ 17 ሺህ የሚጠጉ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች መገንባታቸውን፤ ከ30 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ዕድሳት ተደርጎላቸው ለ2019 በጀት ዓመት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች በመገንባታቸው የተማሪዎችን መጨናነቅ መቀነስ ተችሏል ብለዋል፡፡

የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማስጠበቅ ስራዎች በዘላቂነት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰው፤ ወላጆች ለልጆቻቸው ትምህርት ያላቸው ተነሳሽነትና ክትትል መጨመሩ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.