የጠብመንጃ ጊዜ አብቅቷል! የመደመር መንግሥት የይቅርታ ምዕራፍ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ ዓመት ዋዜማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታራሚዎች በመንግሥት ምሕረት ማግኘታቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከግጭትና ከጉልበት ርምጃ ወደ የሐሳብ ልዕልና መሸጋገሩን የሚያሳይ ታሪካዊ ምዕራፍ ሆኖ ተመዝግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2019 አዲስ ዓመትን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሀገራዊ ምክክሩ ያስገኛቸውን ድሎች እና የመደመር መንግሥት ለሰላም ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት በግልጽ አሳይተዋል።
የኢትዮጵያውያን የድል ምዕራፍ የሆነው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያውያን ተመካክረው ወደ አንድ አቋም ሊደርሱ አይችሉም የሚለውን የተሳሳተ ትርክት አክሽፎ፤ በብዝሃነት ውስጥ የጋራ መግባባት ያስገኘ ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አሁን ያለንበት ወቅት የብዕርና የሐሳብ ጊዜ እንጂ፤ የጠብመንጃ እና የጉልበት ጊዜ አይደለም በማለት በኢትዮጵያ የጠብመንጃ ጊዜ ማብቃቱን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ይህንንም መሰረት በማድረግ የመደመር መንግሥት በአዲሱ ዓመት መግቢያ አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ 600 እስረኞች ከእስር ተፈተው ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ አድርጓል።
ይህ የታራሚዎች የምሕረት ውሳኔ ሁለት መሠረታዊ ዓላማዎች አሉት፡፡ አንደኛ፣ የሀገራዊ ምክክሩን ድል በፍቅር፣ በይቅርታና በሰላም ለመጀመር የተጠየቁትን ጥያቄዎች መሠረት ያደረገ ነው።
ሁለተኛና ዋናው ነጥብ ደግሞ የመደመር መንግሥት ለሰላም ግንባታ ሂደት ያለው ቁርጠኝነት በተግባር የተረጋገጠበት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዚህ የይቅርታ ሂደት የተፈቱ ወገኖች ካለፈው ስህተት በመማር፣ በቀጣይ በሀገራዊ ምክክር ምክረ ሐሳቦች ላይ አዎንታዊና ገንቢ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ማኅበረሰቡም እነዚህ ወገኖች በሀገር ሰላምና ልማት ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማገዝ እና መምከር ይኖርበታል ብለዋል።
በአጠቃላይ የመደመር መንግሥት ያስመዘገበው ይህ አዲስ ታሪክ፤ የጠብመንጃና የግጭት ታሪክ ተዘግቶ፣ በብዕርና በውይይት የምትገነባ የበለጸገች ኢትዮጵያ ዕውን እየሆነች መምጣቷን በደማቅ ቀለም የሚመዘግብ ነው።
በሶስና አለማየሁ