ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት አዳዲስ ትስስሮችን የፈጠረው ብሪክስ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆን በሀገሪቱ የውጭ ግንኙነትና የጂኦ ፖሊቲካ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕዝብ ብዛት፣ በጂኦግራፊያዊ ስፋት እና በኢኮኖሚ ግዝፈት የጎሉ ሀገራትን ያቀፈው ይህ ስብስብ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ፣ የንግድ፣ የፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ መድረኮች ያላትን ተጽዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ሰፊ ዕድል ከፍቶላታል።
የብሪክስ አባልነት ለኢትዮጵያ ሁለገብ የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያፋጥን እና በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ሚዛናዊ ተጽዕኖዋን የሚያጎላ ስትራቴጂካዊ መድረክ ነው።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እና የታሪካዊ ዲፕሎማሲ ባለቤት እንደመሆኗ መጠን፤ የብሪክስ አባልነቷ የታዳጊ ሀገራትን ፍላጎትና ድምጽ በዓለም አቀፍ መድረኮች በግንባር ቀደምትነት ለማንሳት አቅም ይሰጣታል።
ይህም ፍትሃዊ የዓለም ስርዓት እንዲኖር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሀገሪቱ የምታደርገውን ተጽዕኖ ያጎለብታል።
ይህ አባልነት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠንም ሰፊ ዕድል ይፈጥራል። በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ካላቸው እንደ ቻይና፣ ሕንድ እና ብራዚል ካሉ ሀገራት ጋር ያለውን የሁለትዮሽና የባለ ብዙ ወገን የንግድ ትስስር ያጠናክራል።
የግብርና፣ የማዕድን እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ያለ ንግድ እገዳና ኮታ ወደ አባል ሀገራት ገበያ በጥራትና በብዛት በመላክ የውጭ ምንዛሬ ገቢን ማሳደግ ይቻላል።
ከንግድ ግንኙነት ባሻገር፤ የግልና የመንግሥት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ወደ ኢትዮጵያ እንዲሳብ በማድረግ ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ከተለመዱት የምዕራባውያን የፋይናንስ ተቋማት ጎን ለጎን፤ የብሪክስ አባልነት አዳዲስና ተለዋዋጭ የፋይናንስ አማራጮችን ይዞ መጥቷል፡፡
ከእነሱም ዋነኛው ብሪክስ ያቋቋመው አዲሱ ልማት ባንክ ለትልልቅ የመሠረተ ልማት፣ የኃይል፣ የትራንስፖርትና የከተማ ልማት ፕሮጀክቶች ያለ ፖለቲካዊ ጫናና ቅድመ ሁኔታ የብድር እና የፋይናንስ ድጋፍ ለማግኘት መንገድ ይከፍታል።
በአባል ሀገራት መካከል በሀገር በቀል መገበያያ ገንዘቦች የንግድ ልውውጥ የማድረግ እንቅስቃሴ በሀገሪቱ ላይ ሊፈጠር የሚችል የውጭ ምንዛሬ ጫና በእጅጉ ለማቃለል ይረዳል።
የዲጂታል ዘመን ኢኮኖሚን ለማዘመን የቴክኖሎጂ ሽግግር ወሳኝ በመሆኑ፤ በዲጂታል ኢኮኖሚ እና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በታዳሽ ኃይል እንዲሁም በግብርና ቴክኖሎጂ ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ከአባል ሀገራቱ ጋር በቅርበት እንድትሰራ ዕድል ይሰጣል፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነት በጂኦፖሊቲካ፣ በንግድ፣ በፋይናንስ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የተደቀኑ ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ የሚገባትን ስትራቴጂካዊ ቦታ እንድትይዝ የሚያስችል የታሪክ ምዕራፍ ነው።
በመልካም ፈቃዱ