የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ማረጋገጥ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው – አቶ ቀጀላ መርዳሳ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ማስመለስ ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዳይ ነው አሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቶችና ስፖርት አማካሪ ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ።
የአዲስ አበባ አመራር አካዳሚ የዓባይ ወንዝና የባሕር በር ጉዳይን በተመለከተ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።
አቶ ቀጀላ መርዳሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ የባሕር በር ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ የጸጥታ፣ የኃይል አቅርቦትና የንግድ ትስስር ጋር የተቆራኘ ነው።
ቀይ ባሕር ከዓለም አቀፍ የንግድና የኃይል ማጓጓዣ መስመሮች ጋር የተሳሰረ መሆኑን ገልጸው፥ ለኢትዮጵያ የንግድ ተደራሽነት፣ የሎጂስቲክስ አቅም፣ የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነትና ጸጥታ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
ለኢትዮጵያ የባሕር በር ብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትና የቀጣናውን ሰላም የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል።
የአመራር አካዳሚው ፕሬዚዳንት ጣሰው ገብሬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በባሕር በር ዙሪያ የሚደረጉ ምርምሮች ብሔራዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ የጎላ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።
የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ለመመለስ ምሁራን ምርምር በማካሄድ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀው፤ ጥናታዊ ግኝቶቻቸው ወደ ፖሊሲ ተቀይረው ብሔራዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ ሊውሉ ይገባል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በመልክዓ ምድር አቀማመጥና መሰል ጉዳዮች ምክንያት ቀይ ባሕርን የመጠቀም መብት እንዳላት የተናገሩት ደግሞ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ናቸው፡፡
የቀይ ባሕር ጉዳይ የኢትየጵያ ብሔራዊ አጀንዳ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በቅድስት አባተ