በክልሉ ለመስቀል በዓል የቁም እንስሳት እና የፍጆታ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ቀርበዋል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለመስቀል በዓል የቁም እንስሳት እና የፍጆታ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ቀርበዋል አለ የክልሉ ንግድ እና ገበያ ልማት ቢሮ፡፡
የቢሮው ኃላፊ ባዩሽ ተስፋዬ (ዶ/ር) ለፋና ዲጂታል እንደገለፁት÷ የመስቀል በዓል በሰፊው ከሚከበርባቸው ክልሎች አንዱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ነው፡፡
በክልሉ የመስቀል በዓል በድምቀት የሚከበር መሆኑን ጠቅሰው በዓሉን አስመልክቶ የምርት አቅርቦት ችግር እንዳይኖር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል፡፡
በዓሉን ተከትሎ የቁም እንስሳት ግብይት በስፋት እንደሚከናወን የገለፁት ኃላፊዋ ከህብረት ስራ ማህበራት ጋር በመተባበር ለበዓሉ ከ70 ሺህ በላይ በሬዎችን እና ከከ100 ሺህ በላይ በግ እና ፍሎችን ማቅረብ ተችሏል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በዓሉን ተከትሎ ሊከሰቱ የሚችሉ የዋጋ ጭማሪ፣ የምርት እጥረትና ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል የፍጆታ ምርት በሁሉም የሰንበት ገበያዎች በበቂ ሁኔታ እየቀረበ እንደሚገኝ አስታዉቀዋል።
በዕርድ ወቅት የቆዳና ሌጦ ምርት በጥንቃቄና በጥራት ለገበያ እንዲቀርቡ እንዲሁም ማህበረሰቡ በየአካባቢዉ የቆዳና ሌጦ ምርት በሕጋዊ መንገድ ለሚረከቡ ተረካቢዎች እንዲያስረክብ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሚኪያስ አየለ