በኦሮሚያ ክልል 21 የነበሩ ዞኖችን በ6 ዞኖች ያዋቀረው አዲሱ አደረጃጀት
አዲስ አበባ፣ መስከረም 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ጨፌ ኦሮሚያ በዛሬው ዕለት ባካሄደው 1ኛ ዓመት 7ኛ የሥራ ዘመን 1ኛ መደበኛ ጉባዔው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አስፈጻሚ አካላት የማቋቋሚያ አዋጅን አጽድቋል።
ዛሬ በጨፌው የጸደቀው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አስፈጻሚ አካላት አዋጅ ረቂቅ የመንግሥት አካላትን ቅንጅት የሚያጠናክር ነው፡፡
ሪፎርሙ በሕግ የተደገፈና ሥልጣንን ወደ ታች ለማውረድ ያለመ ሲሆን ÷ ቀደም ሲል 21 የነበሩት ዞኖች ወደ 6 ዞኖች ተዋቅረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ÷ የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጠንካራ ሥርዓትና ጠንካራ መንግሥት ለመገንባት አዲስ ሪፎርም ተግባራዊ መደረጉን አስታውቋል፡፡
በክልሉ በልማት፣ በሰላምና በኢኮኖሚ ዘርፍ የብልጽግና ጉዞውን ለማሳካት በተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡
የተገኙ ውጤቶችን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገርና የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ጠንካራ ሥርዓት ለመገንባት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አስፈጻሚ አካላት የማቋቋሚያ አዋጅ መጽደቁን ጠቁሟል፡፡
ይህም መንግሥት የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ሥርዓት ለመገንባት ያለውን አቋም የሚያሳይ በሕግ የተደገፈ ታሪካዊ ውሳኔ መሆኑን ነው መግለጫው ያስገነዘበው፡፡
ሪፎርሙ በክልል ደረጃ ብቻ የቆየውን አገልግሎት በአዲስ መልኩ ወደ ዞን፣ ወረዳና ቀበሌ ደረጃ ለማውረድ እድል የሚፈጥር ነው፡፡
አዲሱ ሪፎርም በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ የመንግሥት ተቋማትን ቅንጅት የሚያጠናክር ሲሆን ÷ በዚህም ተመሳሳይ ሥራዎች በአንድ ላይ እንዲሰበሰቡ በማድረግ የሕዝብ አገልግሎትን ቀልጣፋና በዘመናዊ መልኩ ለመስጠት ያስችላል፡፡
በአዲሱ አደረጃጀት የተዋቀሩ 6 ዞኖችና ያካተቷቸው አካባቢዎች፡-
1. ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን (ምሥራቅ ሐረርጌና ምዕራብ ሐረርጌ)
2. ደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ ዞን ( አርሲ፣ ምዕራብ አርሲ፣ ባሌ፣ ምሥራቅ ባሌ፣ አሰላ ከተማና ዶዶላ ከተማ)
3. ደቡብ ኦሮሚያ ዞን (ቦረና፣ ምሥራቅ ቦረና፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ ቡሌ ሆራ ከተማ፣ ሞያሌ ከተማና ሻኪሶ ከተማ)
4. ደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን (ቡኖ በደሌ፣ ኢሉ አባ ቦር፣ ጅማ፣ አጋሮ ከተማና መቱ ከተማ)
5. ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን (ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋና ነጆ ከተማ)
6. ማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን ( ምሥራቅ ሸዋ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ እንዲሁም አምቦ፣ ባቱ፣ ሆለታ፣ ሞጆ፣ ሰንዳፋ በኬ፣ ሸኖና ወሊሶ ከተሞች)
እነዚህን አዳዲስ ዞኖች በበላይነት እንዲመሩ በጨፌ ኦሮሚያ የተሰጡት አዳዲስ የሹመት ድልድሎች እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-
• አቶ አብዱራህማን አብደላ፦ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የምስራቅ ኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪ
• አቶ መስፍን መላኩ፦ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የምዕራብ ኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪ
• ዶ/ር ረሻድ ከማል፦ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪ
• ዶ/ር መንግሥቱ በቀለ፦ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የማዕከላዊ ኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪ
• አቶ አህመድ ኢድሪስ፦ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የደቡብ ምስራቅ ኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪ
• አቶ አህመድ ሀጂ፦ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የደቡብ ኦሮሚያ ዞን አስተዳዳሪ