የትኬት ዋጋ ጭማሪው ፍትሃዊ ነው – የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የትኬት ዋጋ ጭማሪው ፍትሃዊ ነው አሉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ፡፡
አቶ ክፍሌ ሰይፈ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን እንደገለጹት ሊግ ካምፓኒው የስታድየም መግቢያ የዋጋ ማሻሻያ ያደረገው በክለቦቹ ፍላጎት ነው፡፡
አክሲዮን ማህበሩ ገቢውን ለማሳደግ ነው የዋጋ ጭማሪ ያደረገው በሚል የሚሰራጨው መረጃ የተሳሳተ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አክሲዮን ማህበሩ ከስታድየም ገቢ ምንም ብር እንደማያገኝ ጠቁመው፤ ሙሉ ገቢው የክለቦች መሆኑን ደጋፊዎች ማወቅ አለባቸው ብለዋል።
የዋጋ ጭማሪው የተጋነነ ነው ብለን አናምንም ያሉት ስራ አስኪያጁ ዝቅተኛ አቅም ያላቸው ደጋፊዎች ከስታድየም እንዳይርቁ ከግምት ውስጥ የገባ ውሳኔ መወሰኑን አብራርተዋል።
ይህ ጭማሪ ሲደረግ በምስራቅ አፍሪካ ያሉ ሊጎችን በደንብ መመልከታቸውን ገልጸው፤ ዝቅተኛው የትኬት ዋጋቸው አንድ ዶላር ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ የክለቦች ወጪ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ የዋጋ ማስተካከያ ክለቦችን ለማገዝ የተደረገ ነው ብለዋል።
በሰለሞን በቀለ