Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ልማት ዘላቂ ጉዞ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የጀግንነት ታሪክ፣ የተፈጥሮ ውበት፣ የብዝኃ ሕዝብ እና ባህል መገኛ ታላቅ ሀገር ናት።
እነዚህን ሃብቶች ወደ ዘላቂ ልማትና ብልጽግና ለመቀየር በጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም የያዘ ርዕይና የተቀናጀ ተግባር ይጠይቃል።
የመደመር መንግሥት የልማት ርዕይም ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶችን ከተለያዩ ከፋፋይ ትርክቶች አላቅቆ የጋራ ብሔራዊ ኩራትና የኢኮኖሚ እድገት ምንጭ ማድረግ ነው።
ይህም የሀገሪቱን ቅርሶች መጠበቅ ማልማት ለትውልድ ማስተላለፍና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ማዋል የሚያስችል ስትራቴጂያዊ የአመራር ሥርዓት ነው።
ለዚህም የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የሶፍ ዑመር ዋሻ፣ የፋሲል ግንብ፣ የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥትና ሌሎች ታሪካዊ ቅርሶች የጋራ ብሔራዊ ሃብትነታቸው ተጠብቆ ለቱሪዝምና ለኢኮኖሚ እድገት እንዲውሉ ማድረግ አስችሏል፡፡
ይህ ተግባር ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባሻገር ቅርሶችን ማደስና ለሕዝብ ጉብኝት ማቅረብ፤ ያለፈውን ታሪክ ከዛሬው እንዲሁም ከሚመጣው የልማት እድል ጋር የሚያገናኝ ድልድይ ነው።
በ«ገበታ ለሀገር»ና «ገበታ ለትውልድ» መርሃ ግብሮች እንዲሁም ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ኮይሻ፣ የባሌ ተራሮችና ሌሎች የተፈጥሮ መስህቦችን ለቱሪዝም መዳረሻነት ይበልጥ ሳቢ ያደረጉ ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን የኢኮ-ቱሪዝም አቅም በእጅጉ ያሳደጉ ሀብቶች ናቸው፡፡
አንድነት ወዳጅነት እና እንጦጦ ፓርኮች እንዲሁም በኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የተሰሩ የሀገሪቱ ከተሞች ውበትን ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅም ጋር የማስተሳሰር ጥረት አካል ናቸው።
የወንዝ ዳርቻ ልማቶች፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች እንዲሁም የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች ለነዋሪዎች የመዝናኛ አማራጭ ከመፍጠር ባለፈ ለንግድ፣ ለአገልግሎትና ለቱሪዝም ዘርፎች አዳዲስ ዕድሎችን ከፍተዋል።
የዓድዋ ድል መታሰቢያ የቀደምት ኢትዮጵያውያን ታሪክ የተሰነደበት ሳይንስ ሙዚየም በአንጻሩ ዘመኑን በቴክኖሎጂ የዋጀ ስልጣኔ መገኛ በመሆን የከተማዋን የጉብኝት አማራጮች ያሰፋሉ።
ቱሪዝም ዓለም አቀፍ እውቅናን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ እና ኢኮኖሚን ማነቃቂያ ነው፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ የሆቴል፣ የትራንስፖርት፣ የኪነ ጥበብና የባህል እንዲሁም ሌሎች የቱሪዝም ዘርፎችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማዘመን የሀገሪቱን መዳረሻዎች ለዓለም ማስተዋወቅና የጎብኚዎችን ተሞክሮ ማሻሻልን በትኩረት እየተሰራችበት ትገኛለች፡፡
የዲጂታል መድረኮችን በመጠቀም የሀገሪቱን ታሪክ፣ ባህልና ተፈጥሮአዊ ውበት ለዓለም ማስተዋወቅ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የሚያግዝ ተግባር ነው። ይህ መንገድ ከዘመናዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ዕድሎች ጋር በቀጥታ ያገናኛል።
የእንግዳ አቀባበል፣ የቅርስ ጥበቃና የሀገር መልካም ገጽታ ግንባታ የሁሉም ዜጎች ድርሻ እንደመሆኑ በዚህ ረገድ የግሉ ዘርፍ ባለሀብቶች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጭምር በተቀናጀ መልኩ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
የመደመር መንግሥት የኢትዮጵያን ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ሀብቶች ማልማትና ለኢኮኖሚ ዕድገት ማዋል የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ የሚያፋጥን ምሰሶ አድርጎ እየተጠቀመበት ይገኛል።
ትልቅ ሀገር እና ህዝብን የሚመጥን ውጤት ለማስመዝገብ ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀደም፣ የዜጎችን ተሳትፎ ማጠናከርና ሀብቶችን በዘላቂነት ማልማት ወሳኝ ነው።
በምሕረት ደምሴ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.