የኢትዮጵያና ሩሲያ ስትራቴጂካዊ ትብብር የሀገራችንን የብልጽግና ጉዞ በእጅጉ የሚያፋጥን ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያና ሩሲያ ስትራቴጂካዊ ትብብር የሀገራችንን የብልጽግና ጉዞ በእጅጉ የሚያፋጥን ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በሞስኮ እየተካሄደ በሚገኘው 3ኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ በመገኘት መልዕክቴን ማስተላለፍ በመቻሌ ታላቅ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል።
በዚህ ታሪካዊ መድረክ የምናሳልፋቸው ውሳኔዎች ተጨባጭ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የጋራ ቁርጠኝነት እና ትብብር እጅግ አስፈላጊ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ለዘላቂ ብልጽግናዋ እና ለሀገራዊ እድገቷ መሰረት በሆኑ ሶስት ቁልፍ ምሰሶዎች ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች እንደምትገኝ ጠቅሰው፤ እነዚህም በምግብ ዋስትና እና ምርታማነት፣ በአስተማማኝ የኃይል አቅርቦት፣ እንዲሁም በክህሎት እና በዕውቀት ሽግግር ላይ የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያ እና የሩሲያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ፣ በመከባበር እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የጸና ታሪካዊ ወዳጅነት እንደሆነም አስታውሰዋል።
ይህንን ወዳጅነት ይበልጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከሩሲያ ጋር በጋራ በመሆን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የኒውክሊየር ኃይል ማመንጫ ለመገንባት የሚያስችሉ ተግባራትን በቁርጠኝነት እያከናወንን እንገኛለን ነው ያሉት።
ይህ ስትራቴጂካዊ ትብብር የኃይል አማራጮቻችንን ከማስፋት ባለፈ የሀገራችንን የብልጽግና ጉዞ በእጅጉ የሚያፋጥን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሁለቱን ሀገራት ትስስር ከምንጊዜውም በላይ የሚያጠናክር ይሆናል ብለዋል።