የአህጉሪቱ የጋራ ተስፋና የጋራ ዕጣ ፈንታ የሚመከርባት አዲስ አበባ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ የኢትዮጵያ መዲና ብቻ ሳትሆን የአፍሪካውያን የጋራ መዲና፣ የአህጉሪቱ የውይይት፣ የትብብር፣ የዲፕሎማሲና የጋራ መፍትሔ ማመንጫ ማዕከል እየሆነች መጥታለች።
በመደመር መንግሥት የከተማ ልማት ዕመርታ፣ አዲስ አበባ በአጭር ጊዜ ያስመዘገበቻቸው የልማት ስኬቶች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ዓለም አቀፍ የመዳረሻነት አቅሟን ከፍ አድርገዋል።
የተሻሻሉ መሠረተ ልማቶች፣ ዘመናዊ የከተማ ኮሪደሮች፣ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች፣ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች፣ የመንገድና የትራንስፖርት አውታሮች፣ የመዝናኛና የቱሪዝም መስህቦች ከተማዋን ውብ፣ ምቹ፣ ዘመናዊና ለዓለም አቀፍ ኩነቶች ተመራጭ ማዕከል እያደረጉዋት ነው።
ዛሬ አዲስ አበባ የአፍሪካ መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት፣ የቢዝነስ ማኅበረሰቡ፣ የባለሀብቶች፣ የቱሪስቶችና የልማት አጋሮች መገናኛ ስፍራ ከመሆን ባለፈ፣ የአህጉሪቱ የጋራ ተስፋና የጋራ ዕጣ ፈንታ የሚመከርባት መድረክ ናት።
ይህም የኮንፈረንስ ቱሪዝምን በማሳደግ፣ የከተማዋን ኢኮኖሚ በማነቃቃት፣ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠርና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን በማጠናከር ረገድ ትልቅ አቅም ነው።
አድዋ የአፍሪካ አንድነት፣ ነፃነትና የጋራ የወደፊት ራዕይ ምልክት ነው። የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲስ አበባ፣ በታሪካዊው የጥቁር ሕዝቦች የድልና የነፃነት ምልክት በሆነው የአደዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ጉባኤ ማካሄዳቸው ከተራ የስብሰባ ቦታ ምርጫ በላይ ጥልቅ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና አህጉራዊ ትርጉም አለው።
አድዋ አፍሪካውያን በአንድነት፣ በጀግንነትና በራስ የመወሰን አቅም የቅኝ ግዛትን ምኞት ያከሸፉበት፣ ለጥቁር ሕዝቦችም የክብርና የኩራት ታሪካዊ መሠረት የጣሉበት የድል ታሪክ ነው።
ዛሬ በዚሁ ታሪካዊ ሥፍራ የአፍሪካ የፖለቲካ ኃይሎች መሰባሰባቸው፣ ያለፈውን የጋራ ድል በማስታወስ የአህጉሪቱን የጋራ ፈተናዎች በውይይት፣ በመግባባትና በትብብር ለመፍታት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ከከንቲባ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ይህም አዲስ አበባ የአፍሪካ የነፃነት ታሪክ መዲና ብቻ ሳትሆን፣ የፖለቲካ ውይይት፣ የአህጉራዊ መግባባት፣ የጋራ መፍትሄና የተባበረ የወደፊት ራዕይ ማዕከል መሆኗን የሚያረጋግጥ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።
አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስና ውብ እየሆነች፣ የታሪክና የባህል እሴቶቿን ከዘመናዊ የከተማ ልማት ጋር አጣምራ፣ ለፖለቲካዊ፣ ለዲፕሎማሲያዊ፣ ለኢኮኖሚያዊ፣ ለባህላዊ፣ ለሳይንሳዊና ለስፖርታዊ ኩነቶች ተመራጭ ማዕከልነቷን እያጠናከረች ትገኛለች።
ይህ የከተማ ውበት ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ አንድነትን፣ ትብብርንና የጋራ ብልጽግናን የሚያጎለብት ታላቅ ራዕይ ነው።
አዲስ አበባ፤ ሀገራት እና አለምአቀፍ ተቋማት የሚገናኙባት፣ የሚመክሩባት፣ የጋራ መፍትሔ የሚያፈልቁባት፣ ዓለም የሚሰበሰብባት የአፍሪካ የጋራ መዲና ናት፡፡