Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ የልማት አቅም እውን እንዲሆን የሴቶች ተሳትፎና የአመራርነት ሚና ሊጎለብት ይገባል – ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ የልማት አቅም እውን እንዲሆን የሴቶች ተሳትፎና የአመራርነት ሚና ሊጎለብት ይገባል አሉ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ።

2ኛው የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ “እድገትን ማስተዳደር፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአፍሪካ ኢኮኖሚ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ንድፍ አውጪዎች ናቸው” በሚል መሪ ሀሳብ በዛሬው ዕለት በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም መካሄድ ጀምሯል፡፡

በዚህ አህጉራዊ መድረክ ላይ ሚኒስትሮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ የፓርላማ አባላት፣ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ወጣቶችና ሴቶች፣ የልማት አጋሮች ተወካዮችና ዲፕሎማቶች እየተሳተፉ ነው፡፡

በጉባኤው የዛሬ ውሎ የአፍሪካ የሴቶች የፖለቲካ አመራር ጉባኤና የወጣቶች የፖለቲካ መድረክ እየተካሄደ ነው።

ወ/ሮ ሸዊት ሻንካ በመድረኩ እንዳሉት፤ የአፍሪካ የልማት አቅም እውን እንዲሆን የሴቶችና ልጃገረዶች ተሳትፎና አመራርነት ሚና ከመቼው ጊዜ በላይ ሊጎለብት ይገባል።

ዓለም በማይገመቱ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች እያለፈች መሆኗን ጠቅሰው፥ ይህ ሁኔታ ለአፍሪካ ዕድልና ስጋት ይዞ መምጣቱን አስገንዝበዋል።

የአህጉሪቱ የልማት አቅም ለመጠቀም ቁርጠኛና ራዕይ ያለው አመራርና ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ ወሳኝ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ሴቶችን ያገለለ ማንኛውም ጥረት ውጤት እንደማያመጣ ገልጸው፤ በሴቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ለአፍሪካ ዘላቂ ልማት መሠረታዊ መሆኑን አመልክተዋል።

በመደመር መርህ የሚመራው ኢትዮጵያ የስልጣኔ ትልም ሴቶች እኩል ተሳታፊዎችና የሀገራዊ ለውጥ ቀያሾች እንዲሆኑ እየሠራች መሆኑን ገልጸዋል።

ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የሴቶች የአመራርነት ተሳትፎ 50 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው፤ ሀገሪቱ ሴቶችን በማካተት ብቻ ሳትወሰን በፖሊሲ ቀረጻና በሀገራዊ ለውጥ አመራር ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና አሳድጋለች ብለዋል።

ይህ ለውጥ ራዕይ ያለው አመራር ውጤት መሆኑን በመግለጽ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ተምሳሌት እየሆነች መጥታለች ነው ያሉት።

በአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአመራር መዋቅሮች ውስጥ የሴቶች የአመራር ሚና መጎልበት እንዳለበት አስገንዝበው፤ ሴቶችና ልጃገረዶች ያለምንም እንቅፋት መሪ፣ ስራ ፈጣሪዎች፣ ሳይንቲስቶችና የቴክኖሎጂ ፈጠሪዎች ሆነው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ምቹ አውድ ሊፈጠር ይገባል ብለዋል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በመሳፍንት ብርሌ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.