ከ144 ሺህ በላይ ደንበኞች ስማርት ቆጣሪ ተጠቃሚ ሆኑ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ144 ሺህ በላይ ደንበኞች ስማርት ቆጣሪ ተጠቃሚ ሆነዋል አለ የኢትዮዽያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት።
የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አንዋር አብራር ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ ከተቋሙ ዘመናዊ የአሰራር ማሻሻያዎች መካከል አንዱ እና ዋናው በሀገሪቱ እየተተገበረ ያለውን የዘመናዊ ኤስ.ቲ.ኤስ ቆጣሪ ቴክኖሎጂ በሥፋት ለማዳረስ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ተቋሙ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በመላ ሃገሪቱ ለሚገኙ 144 ሺህ 388 ኤስ.ቲ.ኤስ ቆጣሪዎችን ለደንበኞቹ ማድረሱን ገልጸዋል።
ከእነዚህ ውስጥ 137 ሺህ 247 ያህሉ የነጠላ ፌዝ ተጠቃሚ ደንበኞች መሆናቸውን አመልክተዋል።
የኤስ.ቲ.ኤስ ቆጣሪዎች ከዚህ ቀደም ካሉት ቆጣሪዎች የሚለዩት ደንበኞች በተዘረጉት የክፍያ አማራጮች በቴሌ ብር፣ በሞባይል ባንኪንግ፣ በሲ.ቢ.ኢ ብር፣ በኢንተርኔት ባንኪግ፣ በአዋሽ ብር ፕሮ፣ ኮፔይ ኢ-ብር እና ኤምፔሳ ሳፋሪኮም በጊዜና በቦታ ሳይወሰኑ የኤሌክትሪክ ኃይል መግዛት የሚያስችላቸው መሆኑንም አስረድተዋል።
ከተገጠሙት ቆጣሪዎች መካከል ሲም ካርድ ያላቸውም ጭምር በመኖራቸው አላስፈላጊ የቆጣሪ ንክኪ ሲፈጠር መልዕክት ወደ ሲስተም በመላክ ተገቢውን ርምጃ ለመውሰድ የሚያግዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መሆናቸውንም አስገንዝበዋል።
ይህንን ቆጣሪ ሚጠቀሙ ደንበኞች የኃይል መቋረጥ ቢገጥማቸው አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠትም እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋና ምቹ አሰራር ለመዘርጋት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አጽንኦት ሰጥተዋል።