የኮፕ31 ሁለተኛ ቀን አጀንዳዎችና ኢትዮጵያ ያስመዘገበቻቸው ደማቅ ድሎች
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአንታሊያ፣ ቱርክ እየተካሄደ የሚገኘው 31ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ጉባኤ (ኮፕ31) ሁለተኛ ቀኑን ይዟል፡፡
ጉባኤው በሁለተኛ ቀን ውሎው ትኩረት ያደረገው በታዳሽ ኃይልና በዘላቂ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ ነው።
ዓለም አቀፍ መሪዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች የኃይል ደህንነትን ማረጋገጥ፣ የካርቦን ልቀትን መቀነስ፣ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶችን ማዘመንና ለዘላቂ የኃይል ሽግግር የሚሆን የአየር ንብረት ፋይናንስ ማሳደግ በሚችሉባቸው ነጥቦች ላይም ምክክር እያደረጉ ይገኛሉ።
ይህ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ኢትዮጵያ ከተከተለችው አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ጉዞ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አለው።
ኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን የኤሌክትሪክ ኃይል ከታዳሽ ምንጮች ማለትም ከውሃ፣ ከነፋስ፣ ከጂኦተርማልና ከፀሐይ ኃይል የምታመነጭ ሀገር እንደመሆኗ፤ ለዓለም አቀፉ የኃይል ሽግግር አርዓያ ያደርጋታል።
ይህ የታዳሽ ኃይል አማራጮችን የማስፋፋትና የኤሌክትሪክ አውታረ መረቧን የማዘመን ሥራ፣ ከካርቦን ነፃ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት የተጣለውን ግብ በፍጥነት ለማሳካት በሚያስችላት ደረጃ ላይ ትገኛለች።
በተለይም በትራንስፖርት ዘርፍ የወሰደችው ቆራጥ የፖሊሲ ርምጃ ተጠቃሽ ነው፡፡
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ስትራቴጂና የነዳጅ ተሽከርካሪዎችን ደረጃ በደረጃ የመተካት እቅድ፣ በጉባኤው ከተነሱት ዋና ዋና የአየር ንብረት መፍትሔዎች ጋር የሚጣጣም ነው።
በተጨማሪም በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል አፈርና ውኃን በመጠበቅ፣ የካርቦን ልቀትን በመቀነስና የብዝሃ ሕይወትን በመጠበቅ ረገድ ውጤት ያስመዘገበው የአረንጓዴ ዐሻራ ሌላኛው አብነት የሚሆን ተግባር ነው፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይታለች፡፡
እነዚህ ውጤታማ አፈጻጸሞች ኢትዮጵያ የኮፕ32 ጉባኤን በስኬት ለማስተናገድ ለምታደርገው ዝግጅት ትልቅ መሠረት ናቸው።
ጉባኤው የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲዎቿን ለዓለም ለማሳየት፣ አህጉራዊ የአየር ንብረት መሪነቷን ለማጠናከርና ለታዳሽ ኃይልና መሠረተ ልማት ዝርጋታ የሚሆን ዓለም አቀፍ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ አጋርነትን ለመሳብ ትልቅ እድል ይፈጥራል።
በኮፕ31 የተደረጉ የፖሊሲ ውይይቶችን ወደ ተጨባጭ ተግባር ለመለወጥ ሀገራዊና አህጉራዊ አቅምን ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነ ይታመናል፡፡
ሁነቱ ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማትና የኤሌክትሪክ ትራንስፖርት ስኬቶቿን ማጠናከር እንዲሁም መዋቅራዊና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማፋጠን ለአፍሪካና ለዓለም የአየር ንብረት ቀውስ ተጨባጭ መፍትሄ የሚያመጣ አጀንዳ ለማቅረብ ሁነኛ መድረክ ነው፡፡
በቱርክ አንታሊያ በተጀመረው የኮፕ31 ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ልኡካን በንቃት እየተሳተፈ ሲሆን፤ በሁነቱ ላይ የተከፈተው የኢትዮጵያ ፓቪሊዮን ሀገሪቱ በዘርፉ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎችንና የቱሪዝም መስህቦችን ለማሳየት እድል ፈጥሯል፡፡
በተጨማሪም ከተለያዩ ሀገራት ተወካዮችና ባለሙያዎች ጋር ትብብሮችን ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ለመወያየት የሚያስችል ምቹ መድረክ ነው፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ