Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ተጽዕኖ ፈጣሪነትና የአየር ንብረት ተሟጋችነት፤ በCOP ጉባኤዎች ላይ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ቀደም ባሉት የCOP ጉባኤዎች ላይ፣ በተለይም የ2015ቱ የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት እንዲሳካ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ቡድን በመምራት ታሪካዊና ቁልፍ ሚና ተጫውታለች።
ኢትዮጵያ በታሪክ ለአየር ንብረት መዛባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ የበለጸጉ ሀገራት ለታዳጊ ሀገራት የገንዘብና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዲያደርጉ በተከታታይ ትሟገታለች።
ሀገሪቱ ከተራ ተሳታፊነት ባለፈ የድርድር አጀንዳዎችን በመቅረጽና ዓለም አቀፍ መግባባትን በመፍጠር ትልቅ ተጽዕኖ በመፍጠር የአፍሪካን የጋራ አቋም በCOP-15 (ኮፐንሃገን 2009) እና በCOP-17 (ደርባን 2011) ላይ ጠንካራ ድርድር አድርጋለች።
ኢትዮጵያ ከCOP19 (ዋርሶ 2013) ጀምሮ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለሚደርሱ ድርቅና ጎርፍ ካሳ የሚከፈልበት «የጉዳትና ኪሳራ ፈንድ» እንዲቋቋም ስትሟገት ቆይታለች።
ኢትዮጵያ የታዳጊ ሀገራትን ቡድን በመምራት የዓለም የሙቀት መጠን መጨመርን ከ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንዳያልፍ የሚደነግገው ታሪካዊ ግብ በፓሪስ ስምምነት ውስጥ እንዲካተት ከፍተኛ ግፊት ማድረጓም አይዘነጋም።
ኢትዮጵያ ከዓለም ሀገራት ቀድማ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ያዘጋጀችውን ጥልቅ ሀገራዊ ዕቅድ ለተባበሩት መንግሥታት በማቅረብ ሌሎች ሀገራትም ተመሳሳይ እርምጃን እንዲከተሉ አርዓያ ሆናለች።
ከCOP-21 በኋላ ባሉት ጉባኤዎችም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በማቅረብ የደን ጭፍጨፋን ለመከላከል የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ጥረቶችን ደግፋለች።
አሁን ላይ ሀገሪቱ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታና በታዳሽ ኃይል ልማት ባስመዘገበቻቸው ውጤቶች በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ድርድሮች ላይ ቁልፍ ሚና እየተጫወተች ነው።
በዚህም ምክንያት በፈረንጆቹ 2025 በብራዚል በተካሄደው የCOP-30 ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራትን ሙሉ ድጋፍ በማግኘት የ2027ቱን COP-32 እንድታስተናግድ ተመርጣለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) የCOP-32 ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙ ሲሆን የዝግጅት ሂደቱንና ዓለም አቀፍ ምክክሮችን በበላይነት እየመሩ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ በCOP-32 በማደግ ላይ ያሉና በአየር ንብረት ለውጥ ይበልጥ ጉዳት ለሚደርስባቸው ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጡ አጀንዳዎችንና የአየር ንብረት ፋይናንስ ጥያቄዎችን ማዕከል ለማድረግ ቃል ገብታለች።
አሁን ላይ በቱርኪዬ እየተካሄደ በሚገኘው የCOP-31 ጉባኤ ላይም በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃንና የደን ሽፋንን ለማሳደግ የተከናወነው የእረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ተግባር በCOP መድረኮች እንደ አርአያ ይቀርባል።
ይህም ኢትዮጵያ ለዓመታት በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ መድረኮች ያደረገችው ጽኑ የዲፕሎማሲ ጥረት እንዲሁም በተግባር የተገለጠ ሥራን በማጉላት በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ዲፕሎማሲ የተቀዳጀችውን የላቀ የፖለቲካ ከፍታና አሸናፊነት በግልጽ የሚያሳይ ድንቅ ማሳያ ነው።
በትዕግስት ግዛቸው
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.