ህጻናትን ማዕከል ያደረጉ የልማት መርሐ ግብሮቻችን
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት ሰው ተኮር የልማት ዕሳቤን መሠረት በማድረግ በሥርዓተ ምግብ፣ በቀዳማይ ልጅነት ክብካቤ፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በትምህርት እና በጤና መሠረተ ልማቶች ላይ የተቀናጁ ፕሮግራሞችን በመተግበር የህጻናት ሁለንተናዊ ዕድገትን በማሻሻል ላይ ይገኛል።
በስርዓተ ምግብ እና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ የትምህርት ቤት መገባ መርሐ ግብር እና የሌማት ትሩፋት በመሳሰሉ ፕሮግራሞች የወላጆችን ኢኮኖሚያዊ ጫና በማቃለል የህፃናትን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማጎልበት ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል፡፡
በቀዳማይ ልጅነት ክብካቤ መርሐ ግብር በኩል ደግሞ በጤና ተቋማት እና በቤት ለቤት ጉብኝቶች አማካኝነት የህጻናትን የአዕምሮ ዕድገት፣ የእናቶችን የሥነ-ልቦና ጤንነት እና የወላጆችን የአስተዳደግ ክህሎት የማሳደግ ሥራ እየተሠራ ነው።
የመደመር መንግሥት በተለይም ለሁሉ ነገሮች መሰረት ለሆነው የቅድመ መደበኛ ትምህርት ልዩ ትኩረት ሰጥቷል፡፡
ህጻናት ለመደበኛ ትምህርት ዝግጁ ሆነው እንዲያድጉና ማህበራዊ ክህሎታቸው እንዲዳብር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ35 ሺህ በላይ የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤቶችና በሥራ ቦታዎች የህጻናት ማቆያ ማዕከላት እንዲቋቋሙ ሰፊ ሥራዎች ሰርቷል።
የአረንጓዴ ዐሻራ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎችም ህጻናት ከተጨናነቀ አኗኗር ወጥተው ንጹህ አየር የሚተነፍሱባቸው፣ በነጻነት የሚጫወቱባቸውና አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉባቸው መናፈሻዎች፣ የህጻናት መጫወቻ ሥፍራዎች እና ደህንነታቸው የተጠበቀ የእግረኛ መንገዶች መገንባታቸው ለአካላዊና አዕምሯዊ ጤንነታቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተራቆተ አካባቢን ከማልማት ባለፈ ለዜጎች ጤና፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እጅግ የጎላ ነው።
በከተሞችም የአረንጓዴ ስፍራዎች፣ መዝናኛዎች እና ፓርኮች መስፋፋት አረጋውያን ንጹህ አየር እያገኙ የሚያርፉበት፤ ሴቶች፣ ሕፃናትና ታዳጊዎች በደህንነት የሚጫወቱበትን፣ የሚዝናኑበትንና ማህበራዊ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበትን አውድ ፈጥሯል።
በየዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች የወደፊቷን ኢትዮጵያ ዕጣ የሚወስኑ ህጻናትን ጤና እና ሁለንተናዊ ዕድገት በመሠረታዊነት ለመለወጥ በሚያስችል መልኩ በተቀናጀ እና በተናበበ መልኩ እየተተገበሩ ነው።
በዛሬው ዕለት የዓለም ህጻናት ቀን “የኔ ቀን፣ የኔ መብቶች፣ የኔ መጻኢ ጊዜ” በሚል መሪ ቃል በዩኒሴፍ አስተባባሪነት የተከበረ ሲሆን በሀገራችንም በሴቶችና ህጻናት ሚኒስቴር አማካኝነት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡
በቴዎድሮስ ሳህለ