Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ብሪክስ – ከኒውዴልሂ እስከ ሞንትሪያል

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በካናዳ ሞንትሪያል በተካሄደው 43ኛው የዓለም አቀፉ አቪዬሽን ድርጅት ጉባኤ ላይ የድርጅቱ ምክር ቤት አባል ሆና ተመርጣለች።
ኢትዮጵያ 133 የአባል ሀገራቱን ድምፅ በማግኘት ለምክር ቤቱ አባልነት የተመረጠች ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም የብሪክስ አባል ሀገራት ለኢትዮጵያ እጩነት ድጋፋቸውን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ከሆነችበት ጊዜ አንስቶ በማዕቀፉ አማካኝነት በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ድሎችን የተቀዳጀች ሲሆን፤ ከአባል ሀገራቱ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነቷን በማጠናከር ዓለም አቀፍ ተደማጭነቷን እያሳደገች ትገኛለች፡፡
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪየሽን ምክር ቤት እጩ ሆና ስትቀርብ ከብሪክስ አባል ሀገራት ያገኘችው ሙሉ ድጋፍ ይጠቀሳል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ ብሪክስን ከተቀላቀለችበት ጊዜ አንስቶ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ያላት የዲፕሎማሲ ተሰሚነትና የተጽዕኖ አድማስ በተጨባጭ እየሰፋ መምጣቱን ከሚያረጋግጡ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡
በተለይም የስብስቡ አባል ሀገራት በጋራና በተናጠል ለኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ ፍላጎቶች እያሳዩት ያለው አጋርነት፤ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ያላትን ውክልናና ተሳትፎ ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረ ይገኛል።
የዚህ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት አንዱ ማሳያ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪየሽን ድርጅት ምክር ቤት ውስጥ ያገኘችው የአባልነት ድል ነው።
ኢትዮጵያ የድርጅቱ መስራች አባል ሀገር ብትሆንም፤ በድርጅቱ የበላይ አመራርና ውሳኔ ሰጪ አካል በሆነው ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ ለማግኘት ሰፊ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች።
ይህ የብሪክስ ድጋፍ በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ በተደረጉ የዲፕሎማሲ ጥረቶች የታገዘ ነው።
በተለይም በሕንድ ኒውዴልሂ በተካሄደው የብሪክስ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ የወጣው የጋራ መግለጫ፤ አባል ሀገራቱ ለኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪየሽን ድርጅት ምክር ቤት እጩነት ያላቸውን ሙሉ ድጋፍ በይፋ ያረጋገጡበት ነበር።
በአፍሪካ አቪየሽን ዘርፍ ግንባር ቀደም ሚና ያላት ኢትዮጵያ በዚህ ዓለም አቀፍ ውሳኔ ሰጪ አካል ውስጥ መካተቷ ለሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለመላው አህጉሪቱ የአቪየሽን ኢንዱስትሪ ፍትሃዊ ውክልና ትልቅ ትርጉም አለው።
የብሪክስ ሀገራት ይህንን የኢትዮጵያን እጩነት በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ መደገፋቸው፤ ጥምረቱ ለአባላቱ ስትራቴጂያዊ ጥቅም የሚሰጠውን ትኩረት በግልጽ ያሳየ ነው።
የብሪክስ ጥምረት ለኢትዮጵያ እያስገኘ ያለው የዲፕሎማሲ ትሩፋት በአቪየሽን ዘርፍ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመቀላቀል ስታደርግ የቆየችው ሂደት አዲስ መነቃቃት እንዲያገኝ ጥምረቱ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል።
በዚያው የኒውዴልሂ ጉባኤ ላይ ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን ያላቸውን ጽኑ ድጋፍ አረጋግጠዋል።
ስብስቡ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል እንድትሆን የሚያደርገው ድጋፍ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማሳደግና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችል ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ አቅም የፈጠረ ነው።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል መሆኗ ከኢኮኖሚያዊ ትብብር ባለፈ የጂኦፖለቲካና የዲፕሎማሲ አቅሟን በእጅጉ እያጠናከረ ይገኛል፡፡
ቀደም ሲል በተናጠል ለማሳካት አስቸጋሪ የነበሩ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎችን በታላላቅ ታዳጊ ኢኮኖሚዎች ድጋፍ ታግዛ ወደ ተግባር መቀየር ችላለች።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪየሽን ድርጅት ምክር ቤት አባልነትን እውን በማድረግ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትነት ለማሳካት ጥረቷን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡
በዚህ ረገድ የብሪክስ ሀገራት ድጋፍ ኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መድረኮች ላይ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ከማድረጉም በላይ ለቀጣይ ብሔራዊ ጥቅሞቿ መከበር አስተማማኝ መደላድል እየፈጠረላት መሆኑን በግልጽ ያመላክታል።
ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ስኬት እየተመዘገበበት በሚገኘው የመደመር መንግሥት የዲፕሎማሲ አቅጣጫ ለነገዋ ትልቅ ስንቅን እየቋጠረች ትገኛለች፡፡
በእመቤት ሲሳይ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.