በደቡብ ኢትዮጵያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን ጨንቻ ዙሪያ ወረዳ በተካሄደው የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ዘመቻው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሕዳር 15 ቀን 2019 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን÷ በዚህም በክልሉ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሕፃናትን ለማስከተብ ዝግጅት መጠናቀቁ ተጠቅሷል፡፡
በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አንደኛ ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በምዕራብ ኦሞ ዞን ጀሙ ከተማ በይፋ ተጀምሯል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ም/ኃላፊ አቶ ሙሉቀን አሰፋ በዚህ ወቅት÷ ከ661 ሺህ 309 በላይ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት በዘመቻው እንደሚከተቡ ተናግረዋል።
ክትባቱ ዕድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናትን ለፖሊዮ በሽታ ከመጋለጥ በመከላከል ከልጅነት ልምሻ በሽታ የሚያድን በመሆኑ፣ ለትግበራው ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ ፖሊዮን ለማጥፋት በተከናወኑ ሥራዎች አመርቂ ውጤት የተመዘገበ ሲሆን ÷ በቀጣይ በሽታውን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት የክትባት ዘመቻዎችን በተቀናጀ መልኩ ማከናወን እንደሚገባ መገለጹንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡