በአክሱም ከተማ ዘላቂ የቅርስ ልማት ሥራ በቀጣዩ ሳምንት ይጀመራል
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአክሱም ከተማ ዘላቂ የቅርስ ልማት ሥራ በቀጣዩ ሳምንት ይጀመራል አሉ የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሀጎስ አብረሃ (ዶ/ር)።
በልማት ሥራው ወደ 230 የሚጠጉ የአክሱም ከተማ ወጣቶች እንደሚሳተፉ የገለጹት ኃላፊው፤ ፕሮጀክቱ ከሕዳር ጽዮን ማርያም በዓል ማግስት እንደሚጀመር ጠቁመዋል።
በትግራይ ክልል የቅርስ ጥበቃንና የቱሪዝም ልማትን ለማጠናከር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የገለጹት የቢሮ ኃላፊው፤ በተለይም በክልሉ የተገኘውን ሰላም ተከትሎ በግጭትና በተለያዩ ምክንያቶች ለጉዳት የተጋለጡ ቅርሶችን የመጠበቅና የመታደግ ሥራ ቅድሚያ እንደሚሰጠው አመልክተዋል።
በዚህም ባለፉት ዓመታት ለአደጋ የተጋለጡ እንደ አክሱም ሐውልት ያሉ ታሪካዊ ቅርሶችን ከጉዳት መጠበቅና ለትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችሉ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
በአሸናፊ ሽብሩ