Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ ግጭት የ12 ዜጎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመተከል ዞን ማንዱራ ወረዳ ድኋንዝ ባጉና ቀበሌ በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ ግጭት የ12 ንጹሃን ዜጎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጋሹ ዱጋዝ ግጭቱ ትናንት ከሌሊቱ 8 ሰዓት አካባቢ መነሳቱን ነው የገለጹት።

ከሟቾቹ በተጨማሪ አንድ ግለሰብ ጉዳት ደርሶበት የህክምና ክትትል እየተደረገለት ይገኛል ብለዋል።

ግጭቱ ሶስት ሰዎች የአንድን ግለሰብ መሳሪያ ነጥቀው በመሰወራቸው መከሰቱን ገልጸዋል፡፡

ይህንን ተከትሎም በቀበሌው ነዋሪ የሆነ መሳሪያ የተነጠቀበት ግለሰብ ቤተሰቦች በፈጸሙት ድርጊት አማካኝነት የሰዎች ህይወት ማለፉን ነው ኃላፊው የገለጹት፡፡

አቶ ጋሹ አጥፊዎችን በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ተናግረዋል።

ኃላፊው እስካሁን ያልተያዙ ግለሰቦችን ወደ ህግ ለማቅረብ የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ እና የክልሉ የጸጥታ አካላት እየሰሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የተከሰተው ድርጊት በግለሰቦች መካከል የተፈጠረ ቢሆንም ከጀርባ ተልዕኮ ያላቸው ኃይሎች መኖር አለመኖራቸውን ለማጣራት ምርመራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው በሁሉም የጸጥታ አስከባሪዎች አማካኝነት የማረጋጋት ስራ እየተከናወነ በመሆኑ ህብረተሰቡ ባለበት ተረጋግቶ የዕለት ተዕለት ስራውን እንዲሰራም ጥሪ ማቅረባቸውን ከመተከል ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.