የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ቀሪ አቅምን በመጠቀም መከላከል ይገባል – ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ
አዲስ አበባ፡ ጥቅምት 3 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ የተመራ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በክልሉ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በበርሃ አንበጣ መንጋ ወረርሽኝ የተጎዱ አካባቢዎችን ተመልክቷል፡፡
በብሔረሰብ አስተዳደሩ ካሉት ሰባት ዞኖች ውስጥ በአምስቱ ዞኖች በሚገኙ 46 ቀበሌዎች ላይ የአንበጣ መንጋው ተከስቶ ጉዳት አድርሷል፡፡
ከዚህ ውስጥ አንዱ ባቲ ወረዳ ሲሆን በወረዳው ካሉት 26 ቀበሌዎች በ21ዱ የአንበጣ መንጋው ተከስቶ ሙሉ በሙሉ ማሳ ላይ በሚገኝ ሰብል ጉዳት አድርሷል፡፡
አንበጣውን ለመከላከል ጥረት ያደረጉት አርሶ አደሮቹም አሁን ላይ ከቁጥጥር ውጭ በመሆኑ መንግሥት በአፋጣኝ እንዲደርስላቸው ጠይቀዋል፡፡
ችግሩ በእኛው አካባቢ እና አንድ ጊዜ ብቻ ተከስቶ የሚያቆም አይደለም ያሉት የአካባቢው አርሶ አደሮች የመከላከል ሥራው ከምንጩ እንዲሆንም ጠይቀዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ ክስተቱን “ቅስም ሰባሪ” ብለውታል፡፡
ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ እና የፌደራል መንግሥት ለተጎጅዎች አፋጣኝ ድጋፍ ማድረግ እና ችግሩን በዘላቂነት የመቆጣጠር ስራ እንደሚጠብቃቸው ተናግረዋል፡፡
ጉዳቱ የደረሰባቸው አርሶ አደሮች የዕለት ጉርስ እንደሚያስፈልጋቸው ያነሱት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጥም ጠቁመዋል፡፡
የተከሰተው ችግር ከባድ በመሆኑ እንደ ሀገር ተመሳሳይ ጉዳት ከደረሰብን በቀላሉ መሻገር ይከብደናልናቀሪ አቅማችንን አሟጠን መከላከል ሥራ ላይ ማዋል ይገባል ማለታቸውን አብመድ ዘግቧል፡፡
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።