Fana: At a Speed of Life!

በምስራቅ ሃረርጌ ዞን ቦረዳ ከተማ የሰው ህይወት ያጠፉ ተከሳሾች በእስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ቦረዳ ከተማ በህግ ጥላ ስር የነበሩ ግለሰብ ላይ አሰቃቂ ግድያ የፈጸሙ ሁለት ተከሳሾች በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
የፍርድ ቤቱ ዳኛ አቶ አሸናፊ ሼዱ ÷ ቅጣቱ የተላለፈው በነፍስ ማጥፋት ወንጀል የተከሰሱት መገርሳ ያሲን እና አረቢ ሻዶ በተባሉ ግለሰቦች ላይ ነው ብለዋል።
ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ጃዋር መሃመድ ተከብቤያለሁ በሚል ካስተላለፈው ጥሪ ጋር ተያይዞ ሰልፍ በመውጣት በከተማው በተፈጠረው ሁከትና ግርግር ላደረሱት የነፍስ ማጥፋት ወንጀልና ንብረት ማውደም ውሳኔው መተላለፉን ዳኛው ተናግረዋል።
ተከሳሾቹ በህግ ጥላ ስር የነበሩ አንድ ግለሰብን በአስገዳጅ ሁኔታ በሃይል በመውሰድ በአሰቃቂ ሁኔታ ስለመግደላቸው በዐቃቤ ህግ ማስረጃ መረጋገጡንም ነው የተናገሩት።
ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን የዐቃቤ ህግ ምስክር ሊከላከሉ ባለመቻላቸውና ወንጀለኛነታቸውም በመረጋገጡ ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ.ም በዋለው ችሎት እያንዳንዳቸው በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ ያስተላለፈው የቅጣት ውሳኔ መሰል የወንጀል ድርጊቶች ድጋሚ እንዳይከሰቱ የሚያስተምርና ህዝቡንም የሚታደግ መሆኑን ዳኛው ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.