Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ በኮቪድ 19 ከሚያዙ ሰዎች ውስጥ 15 በመቶ የሚሆኑት ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል ይገባሉ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 10 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ አሁን ላይ በኮቪድ 19 ከሚያዙ ሰዎች ውስጥ 14 ነጥብ 9 በመቶዎቹ ወደ ጽኑ ህሙማን ክፍል እንደሚገቡ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ የኮቪድ19 ስርጭት ያለበት ሁኔታ እና ከመነሻው ጀምሮ እስካሁን ን ምላሽ በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን ገለጻ ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አስቻለው አባይነህ እንዳሉት ኮቪድ19 በዓለም ጤና ድርጅት የዓለም የጤና ስጋት መሆኑንና ሃገራት ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከመገለጹ አስቀድሞ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ በመግቢያና መውጫ በሮች የሙቀት ልየታና ክትትል በማድረግ ቫይረሱ ሊያስከትለው የነበረውን ችግር በእጅጉ መቀነስ ችሏል።
አሁን ላይ አዲስ አበባ በስርጭቱ ቀዳሚ መሆኗ የተገለፀ ሲሆን ኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።
በኢትዮጵያ ያለውን የቫይረሱን ስርጭት ለማወቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደ የአንድ ወር ሃገር አቀፍ የምርመራ ዘመቻ ከ73 በመቶ በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተለይተዋል ብለዋል።
አሁን ላይ የምርመራ መጠን የቀነሰ ቢሆንም ቫይረሱ የሚገኝባቸው እና ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑም ተነስቷል፤ ባለፉት ሁለት ሳምንት ውስጥ እንደሃገር ያለው የቫይረሱ ስርጭት 10 ነጥብ 4 በመቶ መሆኑም ተገልጿል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ኮቪድ19ኝን ለመከላከል አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅትና መከላከል፣ የህክምናና የላቦራቶሪ ማዕከላትን የማደራጀት ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው ቫይረሱ በሃገሪቱ ከተከሰተ በኋላ የተወሰዱ ጥብቅ እርምጃዎችና የአስቸኳይ አዋጅ መታወጁ ሊከሰት የነበረውን ችግር መቀነስ አስችሏል ነው ያሉት፡፡
ኮቪድ 19ኝን ለመከላከል ተወስደው የነበሩ ጠንካራ ክልከላዎችና እገዳዎች እንደሃገር ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ያነሱት ሚኒስትሯ፥ ይህን ከግምት በማስገባት ቫይረሱን የጥንቃቄ ን ተግባራዊ በማድረግ ክልከላዎቹ እንዲላሉ ተደርጓል ብለዋል።
ከመጋቢት ወር ጀምሮ የተዘጋው ትምህርትም እንዲከፈት የተደረገው ያለውን ተጽዕኖ ከግምት በማስገባት ነው ብለዋል ዶክተር ሊያ።
ነገር ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱና የነበሩ ክልከላዎች መላላታቸው በማህበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የሆነ መዘናጋትን መፍጠሩንም ጠቁመዋል።
አሁን ላይ የተነሱትና የላሉት ክልከላዎች ብሎም ትምህርት መከፈቱ አስፈላጊ በመሆኑ አሁንም ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።
የኮቪድ 19 በኢትዮጵያ አሁንም ስጋት በመሆኑ የወጡ መመሪያዎችን ተግባራዊ ከማድረግ ጋር ተያይዞ የጸጥታ አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
በመግለጫው ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ቦሬኢማ ሃማ ሳምቦ ኢትዮጵያ ለኮቪድ 19 የሰጠችው ምላሽ የሚበረታታ መሆኑን በማንሳት አሁን ላይ ትምህርት እንዲከፈት መወሰኑ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ተማሪዎች ለረጅም ጊዜ ቤት ውስጥ መቀመጣቸው ቫይረሱ ከሚያስከትለው በላይ የአዕምሮና የስነ ልቦና ቀውስ እንደሚያስከትልባቸው በመጥቀስም ትምህርት መጀመሩ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
በሃይማኖት ኢያሱ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.