Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የማዕቀፍ ግዢ ስርዓት በመዘርጋቱ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን ተችሏል

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 23 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሚገኙ ተቋማት የማዕቀፍ ግዢ ስርዓት በመዘርጋቱ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን የከተማ አስተዳዳሩ የመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ አስታወቀ።
 
ኤጀንሲው ከማዕከል ጀምሮ እስከ ክፍለ ከተማ በማዕቀፍ ስምምነት የግዢ ስርዓት እንዲኖር ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ መቋቋሙ ተነግሯል።
 
በዚህም ለተቋማት በማዕቀፍ በመንግስት ግዢ እና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ የግዢ ስርዓት ግዢ በመፈጸሙ ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ቢቂና ገላና ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
 
ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በከተማ አስተዳደሩ ለሚገኙ ተቋማት ወደ 6 ቢሊየን ብር የሚያወጡ የጋራ መገልገያ እቃዎች እና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸው መሳሪያዎች ግዢ መፈጸሙን አስታውቀዋል።
 
እንዲሁም 4 ሺህ 478 አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶች እና 725 አገልግሎት የማይሰጡ ተሽከርካሪዎቸን በሽያጭ በማስወገድ ከ311 ሚሊየን ብር በላይ ለከተማ አስተዳደሩ ገቢ ማስገኘቱን ዋና ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል ።
 
በ2013 በጀት ዓመትም ከ2 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ በዓይነት 128 የጋራ መገልገያ ዕቃዎችን ለመግዛት እቅድ መያዙንም ነው የተናገሩት።
 
በሩብ ዓመቱም 1 ሺህ 200 የመገልገያ እቃዎችን እና 100 የሚሆኑ አገልግሎት የማይሰጡ ተሽከርካሪዎችን በሽያጭ የማስወገድ እቅድ ተይዟልም ነው ያሉት፡፡
 
በዚህም 80 ሚሊየን ብር ገቢ ለማስገባት እቅድ ተይዞ እስካሁን 28 ተሽከርካሪዎችን እና 266 ያገለገሉ መሳሪያዎችን በሽያጭ በማስወገድ ከ5 ሚሊየን በር በላይ ገቢ መገኘቱንም ጠቅሰዋል።
በሲሳይ ጌትነት
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.