የፌዴሬሽን ም/ቤት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁሀን ዜጐች ላይ በደረሰው ጥቃት የተሰማውን ሀዘን ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ዋጋ ቃንቃ ቀበሌ በንፁሀን ዜጐች ላይ በደረሰው አሰቃቂ ጥቃት የተሰማውን ሐዘን ገለፀ፡፡
ይህን መሠል ወንጀል በተደጋጋሚ እየተፈፀመ የዜጎች ህይወት እየተቀጠፈ ይገኛል ብሏል ምክር ቤቱ፡፡
በመሆኑም በእነዚህ ስለሀገርና ስለሰው ልጆች ክብርና ስብዕና በሌላቸው የጥፋት ሃይሎች ላይ መንግስት የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ አለበት ፡፡
መላው የሀገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች መንግስት በእነዚህ የጥፋት ኃይሎችና አሸባሪዎች ላይ ለሚወስደው እርምጃ ከመንግስት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ምክር ቤቱ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን በመግለፅ፤ ለተጎጂ ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን ተመኝቷል፡፡