የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ከዓለም አቀፉ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ጋር በጋራ መስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያየ On Nov 20, 2020 481 አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ ከዓለም አቀፉ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን ቀጠናዊ ማናጀር ሼክ ዑመር ሳይላ ጋር ሁለቱ ተቋማት በጋራ አብረው መስራት በሚችሉባቸው ዘርፎች ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡ ውይይቱ በዋናነት በሰራተኞች መኖሪያ ቤት አቅርቦት፣ በአቅም ግንባታ ስልጠናዎች፣ በመድኃኒት ምርቶች አቅርቦት እንዲሁም ሁለቱን ተቋማት በሚያስተሳስሩ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡ ሰራተኞች በአንድ የመስሪያ ቦታ ተረጋግተው እንዲቆዩ ከማያደርጉ ምክንያቶች አንዱ በየከተሞች የሚስተዋለው የመኖሪያ ቤት እጥረት መሆኑን ያነሱት ሼክ ዑመር ሳይላ ለዚህም የሰራተኞች መኖሪያ ቤት አቅርቦትን በተመለከተ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበ በበኩላቸው ÷ ዓለምአቀፉ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን በመኖሪያ ቤት አቅርቦት ላይ ከዚህ ቀደም ያለው ልምድ ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ገልፀዋል፡፡ በመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ በሐይል፣ በኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን እና በማማከር ዘርፍች አብሮ ለመስራት እንደሚያስችልም ነው የገለጹት፡፡ በቀጣይም ከተቋሙ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ወደ ስራ ለመግባት መዘጋጀታቸውንም አቶ ሳንዶካን ማስታወቃቸውን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ 481 Share FacebookTwitterTelegramWhatsAppEmailViberPrint