በቤንች ሸኮ ዞን ሰሜን ቤንች ወረዳ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ተያዘ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤንች ሸኮ ዞን ሰሜን ቤንች ወረዳ ኬላ ላይ በህገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችንና ገንዘብ መያዙን የወረዳው ፖሊስ አስታውቋል።
የወረዳው ፖሊስ አዛዥ አቶ ሀብታሙ ቡንስ እንደገለጹት በወረዳው በድምሩ 18 የጦር መሳርያ በድብቅ ሲንቀሳቀስ ተይዟል።
የተያዙት የጦር መሳሪያዎችም 10 ታጣፊ እና 8 ባለሰደፍ ክላሽንኮቭ የጦር መሳሪያዎች መሆናቸውንም ገልፀዋል።
ተጠርጣሪዎቹ መሳሪያውን ይዘው በመጓዝ ላይ እንዳሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው የተናገሩት።
ፖሊስ አዛዡ አክለውም የጦር መሳሪያዎቹ በትናንትናው እለት በሰሜን ቤንች ወረዳ በጌንጃ ጊዜያዊ ኬላ አካባቢ ላይ ከምሽቱ 3 ሰዓት ከ30 አካባቢ በተደረገ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በቤት መኪና ውስጥ ተደብቆ ከሚዛን ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ እያለ መያዙን ገልፀዋል።
ህብረተሰቡ እንደዚህ አይነት ህገ ወጥ ተግባራትን እንዲያጋልጥ የወረዳው ፖሊስ አዛዥ አቶ ሀብታሙ ቡንስ ጥሪ ማቅረባቸውን የቤንች ሸኮ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መረጃ ያሳያል።