በ10 ዓመቱ የልማት እቅድ የነፍስ ወከፍ ገቢን ከ2 ሺህ ዶላር በላይ ለማድረስ ታቅዷል
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲሱ የፕላንና ልማት ኮሚሽን የ10 አመት የልማት እቅድ ላይ በኢትዮጵያ ከሚገኙ መገናኛ ብዙኃን ጋር የምክክር ጉባዔ ተካሄዷል።
የፕላንና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር ነመራ ገበየሁ የ10 ዓመቱ እቅድ የጋራ ዕቅድ እንደመሆኑ መጠን የሚዲያ ባለሙያዎች መሳተፋቸው አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በልማት እቅዱ ላይ ከ12 በላይ የመነሻ ጥናቶች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማት፣ የሙያ ማኅበራት፣ ገለልተኛ ባለሙያዎች እና የመንግሥት ተቋማት ተሳትፎ እንደነበራቸው የተነሳ ሲሆን፣ የሌሎች ሃገራት ልምድ ተወስዶ ኮሚሽኑ ምን እና እንዴት እንደሚሠራ የመነሻ ሐሳብ ቀርቦ ለጠቅላይ ሚኒትር ዐቢይ አሕመድ መቅረቡንም ዶክተር ነመራ አስታውሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም እያንዳንዱ አስፈጻሚ ተቋም የራሱን እቅድ እንዲያዘጋጅ እንደጠቆሙ ገልጸዋል፡፡
በልማት እቅዱ መሠረት ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ከ2013 እስከ 2022 ባለው ጊዜ በአማካይ 10 በመቶ እንደሚያድግ አመልክተዋል፡፡
በዚሁ የልማት እቅድ በ10 ዓመት የነፍስ ወከፍ ገቢ በአማካይ በ8 በመቶ እንደሚያድግ፣ በ2022 የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ ገቢ 2 ሺህ 201 የአሜሪካ ዶላር እንደሚደርስ የታቀደ ሲሆን እንዲሁም የድህነት ምጣኔውንም ከግማሽ በላይ ለመቀነስ እቅድ አለ ብለዋል ምክትል ኮሚሽነሩ።
በተጨማሪም ሀገራዊ የከተማ ሥራ አጥነት ምጣኔ በ2012 ከነበረበት 18 ነጥብ 7 በመቶ በ2022 ወደ 9 በመቶ ለመቀነስ እቅድ ተይዟልም ነው ያሉት፡፡
በልማት እቅዱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የመጠጥ ውሃ፣ የጤና አገልግሎት እና ትምህርትም ዋና ዋና አቅጣጫዎች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
በጤና እቅዱ መሠረት አማካይ የመኖር እድሜ ጣሪያን በ2012 ከደረሰበት 65 ነጥብ 5 በመቶ ዓመት በ2022 ወደ 68 በመቶ ከፍ የማድረግ ግብ መጣሉ ተመላክቷል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!