Fana: At a Speed of Life!

ባለሃብቶች ለገበታ ለሃገር የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ነው – ብሔራዊ ሐብት አሰባሳቢ ኮሚቴ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 12 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው ብሔራዊ ኮሚቴ አባልና የባለሃብቶች አስተባባሪ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ እንደተናገሩት ኮይሻ፣ ጎርጎራና ወንጪ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር የሃብት ማሰባሰብ መርኃ ግብር እየተከናወነ ነው።

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚለሙት ሦስቱ ፕሮጀክቶች የክልሎችን፣ የከተማና የቱሪዝም ልማትን ለማስፋት ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የነዚህን ፕሮጀክቶች ሥራ ለማስጀመር እየተካሄደ ባለው የሃብት ማሰባሰብ ተግባር በሁሉም ዘርፍ ያለው የንግድ ማኅበረሰብ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የግሉ ዘርፍ ከጅምሩ ያሳየው ምላሽ አዎንታዊ መሆኑን ያወሱት አምባሳደር ምስጋኑ በሸገር ፕሮጀክቶች የነበረው ተሳትፎና ድጋፍ ለገበታ ለሃገርም ተጠናክሮ መቀጠሉን አብራርተዋል።

በቀጣዩ ሣምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የማጠቃለያ የእራት መርኃ ግብር እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።

በመርኃ ግብሩ ለመሳተፍ በቪ አይ ፒ 5 ሚሊየን ብር በቪ ቪ አይ ፒ ደግሞ 10 ሚሊየን ብር ሲሆን በርካታ ባለሃብቶች ገንዘቡን ገቢ እያደረጉና ቃል እየገቡም ነው ብለዋል።

ቃል የገቡ ባለሃብቶች በቀሪዎቹ ቀናት ቃላቸውን በመፈጸም በመርኃ ግብሩ ተሳታፊ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሮጀክቶቹ ዓለም አቀፍ ቱሪዝምና ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠርና ለባለሃብቱም ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታም አስረድተዋል።

አዳዲስ ሃብት በመፍጠርና የንግድ እሳቤዎችን በማምጣት ለባለሃብቶች ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የመሳተፍ ዕድል ይዘው ይመጣሉም ነው ያሉት።

ባለሃብቶች በሀገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በሚሊየኖች በሚቆጠር ገንዘብ አስተዋጽኦ በማድረግ መሳተፋቸው አዲስ ጅማሬ በመሆኑ የበለጠ እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታዎችን መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቶቹ ኢትዮጵያን በትብብር በማልማት አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመፍጠር እሳቤን ለማሳካት ተምሳሌት መሆናቸውን አምባሳደር ምስጋኑ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በአዲስ አበባ የብሔራዊ ቤተ-መንግሥት፣ ወዳጅነት ፓርክ፣ እንጦጦና መስቀል አደባባይ ፕሮጀክቶች በስኬት መጠናቀቃቸው ለከተማዋና ለሀገሪቷም አዳዲስ ዕድሎች፣ ልምዶች፣ የንግድ ሃሳቦችና እሴቶችን ይዘው መምጣታቸውን አውስተዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.