የፋይናንስ ተቋማት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለሳይበር ደህንነት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 19፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፋይናንስ ተቋማት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለሳይበር ደህንነት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ተገለጸ።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (መደኤ) ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር በመተባበር ለፋይናንስ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በሳይበር ደህንነት ዙሪያ የገንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡
በሥልጠናው መክፈቻ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ባስተላለፉት መልዕክት የሳይበር ምህዳር በየጊዜው ተለዋዋጭ በመሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ለጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆኑ ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡
የሳይበር ጥቃት ወንጀል ነው ያሉት ዶክተር ይናገር ደሴ በተለይም በፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ጥቃት ከመፈፀሙ አስቀድሞ የመከላከል ሥራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አያይዘውም በፋይናንስ ዘርፍ የሚቃጣን ጥቃት ለመከላከል በባለድርሻ አካላት መካከል ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር እንደሚገባ እና ባንኮች ተገቢውን የአሠራር ሥርዓት ሊዘረጉ፣ በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ሊያፈሩ እና ያላቸውን ቴክኖሎጂ በፍጥነት በመፈተሽ ብቃት ያለው መሠረተ-ልማት ሊገነቡ ይገባል ሲሉ ዶክተር ይናገር ጠቁመዋል፡፡
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በበኩላቸው የፋይናንስ ተቋማት ከሌሎች ዘርፎች በበለጠ በቀዳሚነት ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ በመሆናቸው ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለሳይበር ደህንነት ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ስልጠናውም የፋይናንስ ተቋማት ምን ዓይነት የሰው ኃይል፣ የአሠራር ሥርዓት እና ቴክኖሎጂ ሊኖራቸው እንደሚገባ ግንዛቤ ለመፍጠር እና በቀጣይ ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመካላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ መናገራቸውን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለዚህ እውን መሆን በተለይም የዘርፉ አመራሮች የሳይበር ደህንነት ማረጋገጥ የሥራቸው ቁልፍ ጉዳይ አድርገው በተጠያቂነት መንፈስ እንዲሰሩ ዶክተር ሹመቴ አሳስበዋል፡፡
ስልጠናው በዋናነት ስለሳይበር ምንነት፣ ባህሪ እና በሌሎች ከሳይበር ደህንነት ዙሪያ ትኩረት በሚሹ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጠነ ነበር፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!