Fana: At a Speed of Life!

የርዕሰ መሥተዳድሮችና አፈ ጉባኤዎች የምክክር መድረክ በባሕር ዳር እየተካሄደ ይገኛል

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በፌዴሬሽን ምክር ቤት አዘጋጅነት የሚካሄደው የርዕሰ መሥተዳድሮችና አፈ ጉባኤዎች የምክክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

“መልካም ጉርብትና ለኢትዮጵያ ብልጽግና”  በሚል መሪ ሀሳብ ነው የሰሜንና ምዕራብ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የምክክር መድረክ እየተካሄደ የሚገኘው፡፡

በመድረኩ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የቤንሻንጉል ፣ የአፋር፣ የጋምቤላ ርዕሰ መሥተዳድሮችና ምክትል ርዕሰ መስተዳድሮች እንዲሁም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ እና የየክልሎቹ አፈጉባዔዎችም እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ የተጎራባች ክልሎች የእርስ በርስ ግንኙነቶች ሕገ መንግስቱን መሰረት ያደረጉ፣ ፌዴራላዊ ስርዓቱን የሚያጠናክሩ ፣ በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኮሩ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

በተለይም ሰው ተኮርና ሕዝቦችን የሚያቀራርቡና መግባባት የሰፈነባቸው ውጤታማ ግንኙነቶች እንዲጎለብቱ ማድረግ እንዲቻል በእኩልነት፣ በአጋርነት፣ በወንድማማችነት፣ በመከባበር፣ በመተማመንና በመተባበር መርሆዎች መመራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

አያይዘውም በኢትዮጵያ የመንግስታት ግንኙነት ሥርዓትን ለማጎልበት እና በሕዝቦች እኩልነትና መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አገራዊ አንድነት ስር እንዲሰድና እንዲዳብር ከምንጊዜውም በላይ የተጠናከረ ሥራ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሰራል ብለዋል

አክለውም የሕገ መንግሥቱ ዓላማ እውን የሚሆነው በሁሉም ክልሎች በሰላም፣ በልማት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ፣ በሰብዓዊ መብቶች አያያዝና በህግ የበላይነትን ላይ ትኩረት ሰጥተን ስንሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም በተጎራባች ክልሎች አዋሳኝና በሁሉም የሀገሪቱ አከባቢዎች በዜጎች ላይ የሞት፣ የአካል ጉዳት፣ የንብረት ውድመትና መፈናቀል የሚፈጥሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን የመለየትና በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።

በቅርቡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል የጋራ ሰላምና ልማትን ለማጠናከር የ5 ዓመት እቅድ ተዘጋጅቶ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው እንደመልካም ጅማሮ የሚወሰድ መሆኑን አንስተዋል፡፡

አፈጉባኤው መልካም ጉርብትናን፣ እኩልነትን፣ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን እና የጋራ ብልጽግናን ሕዝቡ ድረስ እንዲወርድ በማድረግና ውጤት እንዲያመጣ ለማስቻል የተጠናከረ ሥራ መስራት አስፈላጊ እንደሆነ ማሳሰባቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቡት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በመጨረሻም ”መልካም ጉርብትና ለኢትዮጵያ ብልጽግና”  በሚል መሪ ሀሳብ የሰሜንና ምዕራብ ኢትዮጵያ ተጎራባች ክልሎች የምክክር መድረክ ተሳታፊዎች ተወያይተው አቅጣጫ ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.