በኦሮሚያ ክልል ለጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች ተካሄዱ
አዲስ አበባ፣ ጥር 25፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በመላው የኦሮሚያ ክልል ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተሞች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፎች ተካሄዱ።
የሰልፉ አላማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ለሰጧቸው ጠንካራ አመራር፣ በልማት መልካም አስተዳደር እንዲሁም በዲፕሎማሲ ላስመዘገቡት ድሎች ምስጋና ለማቅረብ እና በቀጣይ ከጎናቸው መሆናቸውን ለመግለፅ ያለመ ነው።
በተለያዩ አካባቢዎች በተደረገው ሰልፍ “በድህረ ለውጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና መንግስታቸው ለተሰሩ ስራዎች እውቅና እንሰጣለን፥ በጉልበትና በሀይል ስልጣን ለማግኘትና ለውጡን ለመቀልበስ የሚሰሩ ቡድኖችን እንኮንናለን፣ የኦሮሞ ህዝብ የአጥፊዎች ዋሻ አይደለም” የሚሉ መፎክሮችን አሰምተዋል።
ፅንፈኝነት የሰላም ፀር ነው ያሉት ሰልፈኞቹ ለሰላም ኖቬል ተሸላሚው መሪ ድጋፋችን ይቀጥላል ብለዋል።
የድጋፍ ሰልፎቹ በምዕራብ ሐረርጌ፣ ምስራቅ ሐረርጌ ዞን በጭሮ ከተማ እና በሀረማያ እንዲሁም በባሌ ዞን እና በሮቤ ከተሞች ተደርገዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ ቄለም ወለጋ ፣ ምዕራብ እና ምስራቅ ወለጋ ዞን በቡኖ በደሌ ዞን እና በበደሌ ከተሞችም ተካሄደዋል፡፡
እንዲሁም በጅማ ዞን ጅማ፣ አጋሮ፣ ሊሙ ኮሳ፣ ሰጠማ፣ ሲግሞ፣ ሰቃ ጮቆርሳ፣ ጌራ፣ ጉማይ በምስራቅ ሸዋ ዞን በሻሸመኔም የድጋፍ ሰልፎቹ ተካሄደው ተጠናቀዋል፡፡
በአርሲ ዞን እንዲሁም በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተለያዩ ከተሞችም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን የሚያወድሱና ለውጡን የሚደግፉ መፈክሮች በሰልፎቹ ተሰተጋብተዋል፡፡