የጡረታ መዋጮ የማይከፍሉ የግል ድርጅቶች የንግድ ፍቃዳቸው እንዳይታደስ የሚያደርግ አሰራር መዘርጋቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ ፣ ጥር 28 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጡረታ መዋጮ የማይከፍሉ የግል ድርጅቶች የንግድ ፍቃዳቸው እንዳይታደስ የሚያደርግ የጋራ አሰራር መዘርጋቱን የግል ድርጅቶች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ መዋጮ ክፍያ 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ማገኘቱን ገልጿል።
አብዛኞቹ የግል ድርጅቶች የሠራተኞቻቸውን የጡረታ መዋጮ በአግባቡ እየከፈሉ ቢሆንም አንዳንዶች ጊዜውን ጠብቀው ያለመክፈል፤ የተወሰኑት ደግሞ የጡረታ መዋጮውን ከነጭራሹ የማይከፍሉበት ሁኔታ መኖሩን ኤጀንሲው አስታውቋል።
የኤጂንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ገመቹ ወዩማ ከጡረታ መዋጮ ጋር በተያያዘ በአንዳንድ ድርጅቶች ላይ የሚስተዋለውን መዘግየትና ለመክፈል አለመፈለግ ችግሮች ለመፍታት በአካል ጭምር በመሄድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም በተለያዩ ምክንያቶች የጡረታ መዋጮ የማይከፍሉ ደርጅቶች እንዲከፍሉና ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ኤጀንሲው ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር ቅንጅታዊ አሰራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል።
በዚሁ መሰረት የጡረታ መዋጮ የማይከፍሉ የግል ድርጅቶች በዓመቱ መጨረሻ የንግድ ፈቃድ እድሳት እንዳይደረግላቸው የሚያደርግ አሰራር ተዘርግቷል ነው ያሉት።
ኤጀንሲው በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከግል ድርጅት ሠራተኞች የጡረታ መዋጮ ክፍያ 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን የገለጹት አቶ ገመቹ፤ ገቢው በስድስት ወራት ለመሰብሰብ ከታቀደው 106 በመቶ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።
ባለፈው ዓመት በኮቪድ-19 ምክንያት በንግድ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እንዳይፈጠር በሚል በተገደበ ጊዜ ውዝፍ ወለድና ቅጣት መነሳቱ አቅም እንደፈጠረላቸው እና የምህረት ጊዜውን በመጠቀም በመክፈላቸው ለዕቅዱ አፈጻጸም ከፍተኛ መሆን አስተዋጽኦ እንዳበረከተ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
“በሌላ በኩል ከሠራተኞቻቸው የጡረታ መዋጮ ቆርጠው ለመንግስት ገቢ የማያደርጉ አንዳንድ ድርጅቶች ለወለድና ለተጨማሪ ቅጣት የሚዳረጉ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል” ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
የሠራተኞቻቸው የጡረታ መዋጮ ገቢ ባላደረጉ ድርጅቶች ላይ በተወሰደ እርምጃ ወለድና ቅጣቱን መክፈል ባለመቻላቸው ኪሳራ ውስጥ ገብተው እስከ መዘጋት የደረሱ መኖራቸውንም ተናግረዋል።
ከግል ድርጅቶች የጡረታ መዋጮ የሚቆረጥላቸው ሠራተኞች ቁጥር 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን መድረሱን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
 
			 
				