Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከተማ በአየር ጥራት መቆጣጠሪያ ቴክኒካል ስራዎች ላይ ስልጠና ተሰጠ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ከሲ40 ከተሞች የአየር ንብረት አስተዳደር ቡድን አባል ሃገራት ጋር በጋራ በመሆን በአየር ጥራት መቆጣጠሪያ ቴክኒካል ስራዎች ላይ ስልጠና ሰጠ፡፡

ትኩረቱን በአየር ጥራት ላይ ባደረገው አውደ ጥናት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ሲሆን ለቴክኒካል ድጋፍ ፕሮጀክት አማካሪዎች በአየር ጥራት መረጃ አስተዳደርና ክትትል ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጥቷል፡፡

የአየር ጥራት መቆጣጠሪያ ቴክኒካል ፕሮጀክት በአዲስ አበባ በከተማ ደረጃ የአየር ጥራት መቆጣጠሪያ መሳሪያ በመግዛት እና በማቅረብ እንዲሁም ለከተማዋ የአየር ጥራት ክትትል ማድረጊያ ስትራቴጂ በማዘጋጀት የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ እና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ከአባል ሃገራቱ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ ከብሄራዊ ሜቲዮሮሎጅ ኤጀንሲ፣ ከፌደራል ትራንስፖርት ቢሮ፣ ከትራንስፖርት ባለስልጣን፣ ከአሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድ ቁጥጥር እና ማረጋገጫ ባለስልጣን፣ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታንት ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

ከአባል ሃገራቱ የተውጣጡ ከኬንያ፣ ጋና እና አሜሪካ እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአየር ጥራት መቆጣጠርና የአየር ጥራት መረጃ አያያዝ ዙሪያ ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከዚህ በፊት የተተከሉ የአየር ጥራት መለኪያ መሳሪያዎች ያሉበት ደረጃ እና በከተማዋ ያለውን የአየር ብክለት መጠን የሚለኩ ተጨማሪ መሳሪያዎችን ለመትከል ውይይት የተደረገ ሲሆን መሳሪያዎቹ ለአዲስ አበባ የሚሆን የአየር ጥራት ስትራቴጂ ለመስራት ይውላሉ ተብሏል፡፡

የሲ40 ከተሞች የአየር ንብረት አስተዳደር ቡድን የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ቁርጠኛ የሆኑ የዓለም ትልልቅ ከተሞችን በብቃት ለመተባበር፣ ዕውቀትን የማጋራት እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትርጉም ያለው፣ ሊለካ የሚችል እና ዘላቂ እርምጃዎችን እንዲነድፉ የሚደግፍ ተቋም ነው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.